ቸል ሊባል የማይገባው የቶንሲል ሕመም

3 Hrs Ago 59
ቸል ሊባል የማይገባው የቶንሲል ሕመም
 
በጉሮሯችን ውስጥ የሚገኙት የቶንሲል ዕጢዎች በጀርሞች ተጠቅተው ሲቆጡ እና ሲያብጡ የሚከሰተው ሕመም ቶንሲል (ቶንሲላይተስ) በመባል ይጠራል፡፡
ቶንሲሎቻችን እንዲቆጡ እንዲሁም እንዲያብጡ በማድረግ የሕመም ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉት ባክቴሪያ ወይም ቫይረሶች መሆናቸውን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንገት በላይ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር አሳዬ ንብረት ይናገራሉ፡፡
የቶንሲል ሕመም በብዙዎች ዘንድ እጅግ የተለመደ እና በእየጊዜው የሚያጋጥም የሕመም አይነት መሆኑን ዶ/ር አሳዬ ንብረት ከኤ ፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
በተለያየ መንገድ ሊጠቃ የሚችለው ቶንሲል በአብዛኛውን ጊዜ በኢንፌክሽን የሚከሰት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በትንፋሽ የሚተላለፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቶንሲል ከመጠን ያለፈ እድገት ሊኖረው እንዲሁም በዕጢ (ካንሰር) ሊጠቃ እንደሚችልም አክለዋል፡፡
የቶንሲል ምልክቶች እንደ ሕመሙ አይነት የተለያዩ መሆናቸውን ዶ/ር አሳዬ ገልጸዋል፡፡
የቶንሲል ከመጠን ያለፈ እድገት እና መሰል ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ ከአተነፋፈስ ጋር የተያያዘ ምልክት እንደሚያሳይ ገልጸው፤ ማንኮራፋት፣ የእንቅል መረበሽ እና አፍ ከፍቶ መተኛት ከምልክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡
የቶንሲል ዕጢ ወይም ካንሰር በሚፈጠርበት ጊዜ የሚታይ እብጠት፣ የቶንሲል መድማት፣ ለመዋጥ መቸገር የመሳሰሉት ምልክቶች እንደሚስተዋሉ አብራተዋል፡፡
ቫይረስ አመጣሹ ቶንሲል በአብዛኛውን ጊዜ በቀላሉ በቤት ሕክምናዎች የሚድኑ መሆናቸውን ዶ/ር አሳዬ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ጨው የተቀላቀለበት ሞቅ ያለ ውኃ እና የሎሚ ጭማቂ ቀላቅሎ ደጋግሞ የጉሮሮን የውስጠኛውን ክፍል በማፅዳት፤ በዝንጅብል የተፈላ ሻይ እንዲሁም ትኩስ ነገሮች ደጋግሞ በመጠጣት ሊድን የሚችል ሕመም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣው የቶንሲል አይነት ግን ከባድ የሆነ ትኩሳት፣ አፍ ተከፍቶ በሚታይበት ወቅት ቶንሲል ላይ ነጭ ነጭ ነገሮች እንደሚስተዋሉ እንዲሁም ንፍፊት መሰል እብጠት ሊከሰት ይችላል ነው ያሉት፡፡
ይህ ከተከሰተ ፀረ ተህዋስያን (አንቲ ባዮቲክ ) መድኃኒቶች መወሰድ ስለሚያስፈልግ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባ ዶ/ር አሳዬ ይመክራሉ፡፡
በባክቴሪያዎች በተለይ 'ስትሬፕኮክስ ፓዮጂነስ' በተባለው ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰተው የቶንሲል አይነት በተለየ ሁኔታ ለከፍተኛ የሕመም ስሜት ከመዳረጉም ባሻገር እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ሰዎች ይህን መሰል ምልክት ካስተዋሉ በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም ማምራት ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
'ፓዮጂነስ' በተባለው ባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣው የቶንሲል ሕመም በአግባቡ እና በወቅቱ ሕክምና ካላገኘ ከኩላሊት መድከም እስከ ኩላሊት ስራውን ሙሉ ለሙሉ ማቆም ደረጃ እንደሚደርስ እንዲሁም የልብ ሕመም ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
አንዳንድ ጊዜ ቶንሲሎች በቀዶ ጥገና ሊወጡ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን የገለፁት ዶ/ር አሳዬ፤ በተደጋጋሚ በባክቴሪያ ኢንፌክሽን የተጠቃ ከሆነ እንዲሁም ከቶንሲል እድገት ጋር ተያይዞ የጆሮ እንዲሁም የሳይነስ ኢንፌክሸን ካለ ቀዶ ጥገናው እንደሚደረግ ነው የጠቀሱት፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top