የኦሮሚያ ክልል አመራር አባላት በየዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት መረባረብ አለባቸው -አቶ ሽመልስ አብዲሳ

3 Mons Ago
የኦሮሚያ ክልል አመራር አባላት በየዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት መረባረብ አለባቸው -አቶ ሽመልስ አብዲሳ

የኦሮሚያ ክልል አመራር አባላት በየዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት መረባረብ እንዳለባቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ።

የኦሮሚያ ክልል የባለፉት ስድስት ወራት የመንግስት ስራ አፈፃፀም ግምገማ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

በዚሁ ጊዜ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት የክልሉ አመራር በተገኙ ስኬቶች ሳይዘናጋ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት መረባረብ አለበት።

ባለፉት ስድስት ወራት የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ማጎልበትና የብድር አቅርቦት፣ ኢንተርፕሩነሮችን ከማፍራት አንፃር የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲሁም ህገወጥነትን ከመከላከል አኳያ የተመዘገቡ ስኬቶችና ውስንነቶችን በአግባቡ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል።

በእቅድ አፈጻጸም ግምገማው ሰላምና ፀጥታን ከማስፈን አንጻር የተከናወኑ ስራዎች፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ያለበት ደረጃና እያገጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ የተወሰዱ እርምጃዎች በአግባቡ ይታያሉ ነው ያሉት።

በዚህም አመራሩ በተገኙት ውጤቶች ሳይዘናጋ የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት እንዲችል በግምገማ መድረኩ ጠንካራ አፈፃፀም የታየባቸውን መስኮች አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ የአፈፃፀም ጉድለት የታየባቸው ዘርፎች ተለይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ ግምገማው ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ፓርቲ የተከናወኑ ተግባራት በአግባቡ ታይተው አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ በየደረጃው ያለው አመራር አባላት የአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን ከማስወገድ አንፃር ያለበት ደረጃ የሚገመገምበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም የፖለቲካ አመራር ሰጪነትና ቁርጠኝነት የታከለበት ርብርብ በማድረግ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ማሳካት ከአመራሩ የሚጠበቅ ቀዳማዊ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል ።

መድረኩ ለቀጣይ ሶስት ቀናት የሚቆይ መሆኑን ከመረሃግብሩ ማወቅ ተችሏል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top