የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

2 Mons Ago
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት ነው - አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፥ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም፥ አውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ብሔራዊ ጥቅሟን አስከብራ ለመዝለቅ ያደረገችውን ጉዞ እና ዲፕሎማሲያዊ ከፍታዋን ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

አውደ-ርዕዩ ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በሳይንስ ሙዚየም መከፈቱን አስታውሰዋል።

ዓላማውም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከጥንት እስካሁን ያለውን ተግዳሮት እና ከፍታ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ ማስረዳት መሆኑን ገልጸዋል።

መጪውን ዲፕሎማሲ ዘመኑን በዋጀ አዲስ የአስተሳሰብ ቅኝት በመቅረጽ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን አስከብራ ለመዝለቅ የሚያስችላትን ፍኖተ-ካርታ ማመላከት ከዓላማዎቹ መካከል ይገኝበታል ብለዋል።

አውደ-ርዕዩ ለ48 ቀናት መቆየቱን ጠቅሰው፤ ከ250 ሺህ በላይ በሆኑ ዜጎች መጎብኘቱንም ጠቁመዋል።

በዚህም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የከተማ እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፤ ከውጭ ሀገራት ደግሞ ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት አውደ-ርዕዩን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።

ከ116 ዓመት በላይ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ታሪካዊ እጥፋቶችን የሚያስቃኝ የመጀመሪያ ቅጽ መጽሐፍም ከአውደ-ርዕዩ ጎን ለጎን መመረቁን ገልጸዋል።

አውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማሳየት የተቻለበት መሆኑን ተናግረዋል።

ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ሥራ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በድኅረ-ለውጥ ወቅት የገጠማትን የውስጥ እና የውጭ ጫና ለመመከት ያደረገቻቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እና ከፍታዎች ማሳየት መቻሉን ጠቁመዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ በብዙ ወጀቦች መሀል ሆና ከዋናው ሀገራዊ ግብ ሳትደናቀፍ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ክብሯን ማስከበር መቻሏን ጠቁመዋል።

የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ተቋማት እንዲሁም ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን በድጋሚ ለማረጋገጥ መቻላቸውንም ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይ "ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" በሚል መሪ ቃል መከናወኑ ይታወሳል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top