የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ ተመለሰ

1 Mon Ago
የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ ተመለሰ

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ምርት ሂደት መመለሱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ አስታወቁ።

በሰሜኑ ግጭት ምክንያት ላለፉት ግዜያት ስራ አቁሞ የቆየው የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ከፍተኛ የርብርብ ስራና በተሰጠው ትኩረት ዛሬ ወደ ስራ መግባቱን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።  

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ኩባንያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ እንዲሁም አዳዲስ ኢንቨስተሮች በፓርኩ ለማምረት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የቅድመ ኢንቨስትመንት ስራዎቻቸውን እያጠናቀቁ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ኮርፖሬሽኑም ኩባንያዎቹ ወደ ምርት ሂደት እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሂደት እንዲገባ፤ ውጤታማነቱ ከፍ እንዲል እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅርበት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ238 ሄክታር መሬት ላይ ተገንብቶ በ2017 (እ.አ.አ) ስራ የጀመረ ሲሆን 15 የማምረቻ ሼዶች እንዲሁም የለማ መሬት ለኢንቨስተሮች ዝግጁ መደረጉን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top