ከተሞቻችን ከብክለት የፀዱ እንዲሆኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎቻችን ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡- ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ

13 Days Ago
ከተሞቻችን ከብክለት የፀዱ እንዲሆኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎቻችን ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡- ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ
ከተሞቻችን ከብክለት የፀዱ እና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ የአረንጓዴ ልማት ስራዎቻችን ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ገለጹ።
 
የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ለዜጎች ንፁህና ጤናማ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችል ክልል አቀፍ ንቅናቄ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ በይፋ ተጀምሯል።
 
"ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ቃል የሚከናወነው መርሐ-ግብር ፤ በቀጣዮቹ 6 ወራት በመላ ሀገሪቱ የሚተገበረው ንቅናቄ አካል ነው።
 
ንቅናቄው በጅግጅጋ ከተማ ብሎም በመላ ክልሉ የፕላስቲክ፣ የውኃ፣ የአየር ፣የአፈር እና የድምፅ ብክለት የሚያስከትሉን ችግሮች መከላከል ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ በመድረኩ ተገልጿል።
 
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ፤ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በየአካባቢው ያለአግባብ በሚወገዱ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ሳቢያ የእንስሳት እና የማህበረሰብ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል።
 
ይህን የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በክልሉ ካሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጀምሮ ወደ ማህበረሰቡ የሚያድግ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ብለዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ደ/ር) ከወራት በፊት በክልሉ በነበራቸው ጉብኝት፤ የአካባቢ ብክለትን የሚቀንሱ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የስራ መመሪያ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።
 
በዮሐንስ ፍስሃ
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top