በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወሱት የመርካቶው ነጻ አውጭ- ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ

12 Days Ago
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወሱት የመርካቶው ነጻ አውጭ- ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወሱት የመርካቶው ነጻ አውጭ- ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ

******

 የወልቂጤ እስታድየም ከአፍ እስከ ገደፉ በሕዝብ ተሞልቷል። ዓላማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ላለፉት ስድስተ ዓመታት ላከናወኑት የለውጥ ሥራ ምስጋና እና ድጋፉን ለመግለጥ ነው። በዚያ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታታሪው የጉራጌ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ዘርዝረዋል፡፡ ‘ጉራጌ ለአንድነት ተምሳሌት መሆኑን፣ ጠንክሮ በመሥራት ዓርአያ መሆኑን፣ አካባቢን ሳይለይ በየደረሰበት ታትሮ በመሥራት ምሳሌ መሆኑን በዚህም ጉራጌን ይዘን እንደማናፍር’ ገልጸዋል፡፡ ጉራጌ በንግዱ ዘርፍ ያበረከተውን አስተዋጽኦ እና የመርካቶን ንግድ ከውጭ ዜጎች ቁጥጥር ነጻ ስላወጡት የጉራጌው ታታሪ ጀግናም አንስተዋል፡፡

ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሷቸው የመርካቶው ነጻ አውጭ እና ንግድ ማራኪው ዐርበኛ ማን ናቸው? ምንስ ሠርተው ተመሰገኑ?

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወደሱት የኢትዮጵያ ባለውለታ ከወልቂጤ እስከ መርካቶ ድል ያስዘከሩ፤ ከጉራጌ ቀዬዎች በመነሳት የአዲስ አበባ የንግድ ማዕከላትን ከውጭ ነጋዴዎች ቁጥጥር እጅ በማውጣት ኢትዮጵያዊያን የንግድ የበላይነቱን እንዲረከቡ ያስቻሉት ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ ናቸው፡፡

 ኢትዮጵያ ውስጥ የችርቻሮ ንግድ የጀመሩት በአብዛኛው የመኖች እንደሆኑ ታሪክ ዋቢ ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ሀገር ነጋዴዎች ግን ቀስ በቀስ እየተስፋፉ የችርቻሮ ንገድ ላይ ተሰማርተው ሁሉንም ነገር እየተቆጣጠሩ መሄዳቸው ሁኔታውን አሳሳቢ አደረገው፡፡ ይህ ሂደት እንዲቀየር እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅትም ፊታውራሪ ሩጋ አሻሜ የተባሉ ለሀገራቸው አሳቢ ልበ ቀና ሰው የችግሩን መፍቻ ቁልፍ አመጡ፡፡

በኢትዮጵያውያን ‘የዓረብ ቤት’ እያሉ ይጠሩአቸው የነበሩት እና በውጭ ዜጎች የተያዙት የንግድ ቤቶች ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳ መሆኑን የተገነዘቡት የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ሀብተወልድ ጥናት ተደርጎ አንድ መፍትሔ እንዲገኝለት ልዩ ኮሚቴ አቋቋሙ።

ጉዳዩን አጥንቶ እንዲያቀርብ የተቋቋመው ኮሚቴ ባካሄደው ጥናትም ከዚህ በኋላ ለውጭ ዜጎች አዲስ የንግድ ፈቃድ እንዳይሰጥ፣ ፈቃድ ወስደው እየሠሩ ያሉት ፈቃዳቸው እስከሚያልቅ ብቻ እንዲሠሩ እና በቀጣይ ፈቃዳቸው እንዳይታደስላቸው የሚል የውሳኔ ሀሳብ አቀረቡ፡፡

የንግድ ሚኒስትሩ ለውጭ ሀገር ዜጎች የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ የሚከለክል አዋጅ የማውጣት አስፈላጊነትን ቢያምኑበትም፣ ንግዱን ሙሉ በሙሉ በሚረከቡ ኢትዮጵያውያን እስካልተተኩ ድረስ የችግሩ የመጨረሻው መፍትሔ አለመሆኑን በማመን ኢትዮጵያውያን ሥራውን የሚረከቡበትን ዘዴ እንዲፈለግ ኮሚቴው ጥናቱን እንዲቀጥል አዘዙ።

የኮሚቴው አባል የነበሩት ፊታውራሪም ሩጋ ከ30 እስከ 40 የጉራጌ ወጣቶች ተመርጠው ብድር ተሰጥቶአቸው በዓረቦቹ የንግድ ቤቶች አካባቢ ሥራ ቢጀምሩ በዓመት ውስጥ ውጤት ያመጣሉ የሚል ሀሳብ አመጡ፡፡ በዚህ ሀሳብ የተደሰቱት አቶ መኮንን ዕቅዱ በአፋጣኝ ሥራ ላይ እንዲውል ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ 

አቶ መኮንን ከንጉሡ ባስፈቀዱት መሰረትም በወጣቱ ሩጋ አሻሜ እና በጓደኞቻቸው ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠው የቀረቡት አርባ የጉራጌ ነጋዴዎች ለያናዳንዳቸው የሥራ መነሻ ገንዘብ ተሰጥቷቸው ሥራ በጀመሩ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሆኑ፡፡

ሕዝቡም ደንበኝነቱን ከነሱ ጋር ስላጠናከረ በትጋት እና በጋለ ስሜት መሥራት ጀመሩ። ከአርባዎቹ ጉራጌዎች መካከል ሰላሳ ሦስቱ በውጭ ዜጎች ተይዞ የነበረውን ንግድ በሙሉ ስለተቆጣጠሩ የውጭ ዜጎች የነበራቸውን ሱቅ እየዘጉ ከየሠፈሩ መውጣት ግዴታ ሆነባቸው።

ጉራጌዎቹ ተጠናክረው ባሳዩት ብርቱ ጥረትም የየመን ዓረቦች አብዛኛዎቹ ሱቆቻቸውን እየዘጉ ወደየሀገራቸው ሲመለሱ ጥቂቶች ደግሞ ሌላ ባላንጣ ደርሶ እስከሚያባርራቸው ወደ ዋናው ገበያ ወደ መርካቶ እየተዛወሩ በልዩ ልዩ የጨርቃ ጨርቅ ንግድ ለመቋቋም ሞክረው ነበር። ሙከራቸው ብዙ ሊያቆያቸው ስላልቻለ እነሱም ቀስበቀስ እየለቀቁ ሄዱ።

የጉራጌዎች ንግድ ሥራ አባት በሆኑት ፊትአውራሪ ሩጋ አሻሜ ሀሳብ አፍላቂነት መርካቶን እና ሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎችን ነጻ ያወጡት ጉራጌዎች፣ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰኑ በኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ የንግድ ሥራ ማስፋፋት መገለጫቸው ሆኖ ቀጠለ፡፡ ፊታውራሪ ሩጋ በዚህ ተግባራቸው በኢትዮጵያ የንግድ ታሪክ ውስጥ ስማቸው በጉልህ ሲነሳ ይኖራል፡፡

ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ ኢትዮጵያ ነጻ ብትወጣም አንድ ብልህ ኢትዮጰያዊ "ገና ያላለቀ ነገር አለ" ብሎ ተናገረ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከወራሪው ነጻ ብትወጣም መርካቶ አሁንም ነጻ አልወጣም ብሎ ስለ ኢኮኖሚ ነጻነት ፊታውራሪ ሩጋ ያደረጉትን ተጋድሎ አድንቀዋል። 

ብሔራዊ ዐርበኝነት እና ውጤቱ በሁሉም የትግል መስክ የሚከፈል መስዋዕትነት መሆኑን ባነሱበት ንግግራቸው መላው ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው አንድነት፣ እድገት እና ብልጽግና የነፊታውራሪ ሩጋ አሻሜን መርህ ስለ ኢትዮጵያ ጥቅም እንዲከተሉ አሳስበዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top