ለትራፊክ አደጋ ስጋት የነበሩ ቦታዎች ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፦ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን

1 Mon Ago 309
ለትራፊክ አደጋ ስጋት የነበሩ ቦታዎች ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፦  የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን
በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለትራፊክ አደጋ ስጋት የነበሩ ቦታዎች ላይ ማስተካከያ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ገለጿል፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ በ5 የሪደር ልማት ላይ ማሻሻያ ተደርጎ የእግረኞች፣ የተሽከርካሪ፣ የብስክሌት መጓዣ የሌለባቸው ቦታዎች እንደተገነቡ ጠቁመዋል፡፡
 
ይህ ለከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ጸጋ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ "ከመንገድ ደህንነት እና የትራፊክ ፍሰት ከማሻሻል አንጻር እና ለዜጎች ምቹ የሆነች ከተማ ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይጫወታል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
 
ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ መንገዶች የሚገነቡት ለተሽከርካሪ ብቻ ነበር የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ የዲዛይን ችግር የነበረበት እንዲሁም ለትራፊክ ፍሰት ማነቆ የፈጠር እንደነበርም አመላክተዋል፡፡
 
ይህን ለማስተካከልም ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን በየአመቱ አደባባዮችን በማፍረስ የትራፊክ ፍሰቱን ለማስተካከል እየሰራ እንደነበረም አንስተዋል፡፡
 
አሁን ግን ይህን ሁሉ ችግር በዘላቂነት የሚፈታ የኮሪደር ልማት መከናወኑን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ክበበው ሚደቅሳ ተናግረዋል።
 
በአዲስ አበባ ይስተዋል የነበረው አንዱ ችግር የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) እንደነበር የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ችግር ለመቅረፍ በኮሪደር ልማቱ 32 አዲስ እና ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ መገንባታቸውን ገልጸዋል።
 
አዲስ 9 የታክሲና የባስ ተርሚናሎች በኮሪደር ልማቱ ተገንብተዋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ አደጋን ከመቀነስ አንጻርም ይህ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
 
የዋና ዳይሬክተሩን ሃሳብ የሚጋሩት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ግርማ በላቸው የኮሪደር ልማቱ የትራፊክ ፍሰቱን እንደሚያሻሽል እና አካል ጉዳተኞችን ብሎም እግረኞችን ያማከለ መሆኑ አደጋንም ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል፡፡
 
መንገዶች መገንባታቸው እና እየተገነቡ መሆናቸው አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመሆን ሳቢና ውብ ከተማ መሆን ያስችላታል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
 
ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ እየተለወጠች ነው የሚሉት ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወ/ሮ ሰናይት ሙሉጌታ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የትራፊክ ፍሰቱን ያሻሽለዋል ብለዋል።
 
ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ አማራጭ ትራንስፖርት ለመጠቀም እና በፍጥነት ካሰቡት ቦታ ለመድረስ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።
 
በሜሮን ንብረት
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top