በኢትዮጵያ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል፤ የትግል፣ የጽናት እና የሕልም ጉልበትን የሚያሳይ ሃይማኖታዊም ታሪካዊም ክስተት ነው።
ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ለማውጣት ያለመችው ዙሪያዋ ጨለማ በነበረበት፣ መንገዶች ሁሉ በተዘጉበት እና ነገሮች ሁሉ አስቸጋሪ በነበሩበት ወቅት እንደነበር ታሪክ ያወሳል።
ማንም በማያስበው እና "አይቻልም፤ አይሞከርም" በሚባልበት ወቅት፣ በጽናት የታገለችው ንግሥት ዕሌኒ ኢየሩሳሌም ተሻግራ መስቀሉን ከተቀበረበት ሥፍራ ለማውጣት በቅታለች።
በአከባበር ሒደቱ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚይዘው ደመራ ታዲያ ለሚታገል፣ ተስፋ ለማይቆርጥ እና እስከ መጨረሻው ለሚጸና ሰው ሕልሙ አንድ ቀን እውን እንደሚሆን የሚያሳይ ትእምርት ነው።
በመስቀል በዓል ወቅት የሚነገረው “እዮሃ” የሚለው ቃል “ይሄዋ” (ተገኘ፤ ተሳካ፤ እውን ሆነ) የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፤ ከበረቱ፣ ከታገሉ እና ከጸኑ የማይሳካ ነገር እንደሌለ የሚያስነዝር ነው።
የመስቀል በዓል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫም ነው። ደመራው ከእንጨት ወደ ችቦ፣ ከችቦ ወደ ደመራ የሚያድግበት መንገድ የመደመርን ኃይል እና ጉልበት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
በተጨማሪም የመስቀል በዓል በተለያየ ባህል እና አከባበር በብዙ ብሔረሰቦች ዘንድ መከበሩ በኅብረ ብሔራዊነታችን ውስጥ ያለውን ነባር ትሥሥር፣ የወል ትርክት እና አንድነት የሚያጎላ ነው።
በመሆኑም በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ደረጃ ደመራ በሚደመርበት እና በሚለኮስበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሀገራቸውን ሊያስቡ የሚገባበት አጋጣሚ ነው።
የሁላችንም ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ወጎች፣ አቅሞች፣ ጸጋዎች፣ ሀብቶች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገች እና የተከበረች ሊያደርጓት እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም።
በእርግጥም ኢትዮጵያ አሁን ላይ እንደደመራው ጎልቶ የሚታይ ብርሃን፣ ከሩቅ የሚታይ ተስፋ እና ልማትን እያሳየች ነው። እናም ለልጆቻችን “ከተደመርን እንደ ደመራው ብርቱ እንሆናለን፤ እንደ ደመራው ከፍ ብለን እናበራለን” የሚል አስተማሪ መልእክት ስናስተላልፍ ከነማሳያዎቹ ጭምር እያሰናሰልን ነው።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: