Search

ለአፍሪካ ዘመናዊ የከተማ ግንባታ ትልቅ ተሞክሮ የሚሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳትና የአረንጓዴ ውበት

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 37

የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት እና የአረንጓዴ ልማት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዘመናዊ የከተማ ግንባታና የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን የ5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆየውን 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በይፋ መክፈታቸው ይታወቃል።

በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከ100 በላይ ከሆኑ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ከሴኔጋል የመጡት ሼይክ ሲዲያ ጋዬ እንዳሉት፣ ጉባኤው የአህጉሪቷን የሕዝብ ጤና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም የአዲስ አበባ ንጽህና፣ ጽዳት፣ ውበትና የመንገዶች ደኅንነት ቀልብን የሚስብ ማራኪ ገጽታ የተላበሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዓለም ዙሪያና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተዘዋውረው የመመልከት ዕድል እንደነበራቸው በመጠቆም፣ አዲስ አበባ ከተመለከቷቸው ከተሞች መካከል በንጽህናዋና በማራኪ የከተሜነት ገጽታዋ እንዳስደመመቻቸው ተናግረዋል።

የከተሞችና የአካባቢ ንጽህና ለሕዝብ ጤና አጠባበቅ ሥርዓት እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ያሉት ተሳታፊው፣ የኢትዮጵያ ተሞክሮም ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በምርጥ ተሞክሮነት የሚቀርብ ነው ብለዋል።

ከናይጄሪያ የመጣችው ዶክተር ሩት ሳቦ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ያስመዘገበችው ለውጥ ቀልብን የሚስብ አስደናቂ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ልማት፣ የፕላስቲክ አጠቃቀምና አወጋገድ የፖሊሲ እርምጃና መሠረተ ልማቶች ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ግብ መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ አስደናቂ የከተሜነት ገጽታ ለበርካታ የአፍሪካ ከተሞች የሥነ-ምኅዳር ደኅንነት ትልቅ ትምህርት የሚያስተላልፍ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የጉባኤው ተሳታፊ ናይጀሪያዊ ዶክተር ኤፎሳ ኤዛሞ ናቸው።

ንጹሕ አካባቢ መኖሩ ለሕዝብ ጤናማ ኑሮን ከማስፈን ባለፈ ማኅበረሰቡ በተሻለ ሁኔታ እንዲኖር፣ እንዲበለጽግና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዘመናዊ የከተሜነት ግንባታ ተሞክሮም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: