የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከ15 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችን የማህበራዊ ሚዲያ፣ የቪዲዮ ማጋሪያ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም የሚገድብ አዲስ የአውሮፓ ህብረት የህፃናት ህግ (EU KIDS Act) ይፋ ለማድረግ መዘጋጀቱ ገልጿል።
ይህ አህጉራዊ ውሳኔ እንደ ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ያሉ አፕሊኬሽኖች የታዳጊዎችን አእምሯዊ ጤና በሚጎዱ አሰራሮቻቸው ላይ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከፖለቲከኞች እና ከወላጆች ከፍተኛ ተቃውሞና ጫና እየበረታባቸው በመጣበት ወቅት የተወሰደ ነው።
ቀደም ሲል እንደ ፈረንሳይ፣ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ግሪክ እና ስፔን ያሉ ሀገራት ህፃናትን ከማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመጠበቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ህጎችን ማውጣት የጀመሩ ሲሆን፣ አዲሱ ህግ ደግሞ በመላው አውሮፓ ህብረት ደረጃ ወጥ የሆነ አሰራርን ለመዘርጋት ያለመ ነው።
አዲሱ ህግ እንደ እድሜ ደረጃቸው የተከፋፈሉ የመተግበሪያ አጠቃቀም ደንቦችን የሚያስቀምጥ ሲሆን፤ ከ13 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት መተግበሪያዎችን መጠቀም የሚችሉት በወላጆች ሙሉ ቁጥጥር ስር ብቻ እንዲሆን ያደርጋል።
ከ13 እስከ 15 ዓመት ላሉ ታዳጊዎች ደግሞ ከማይታወቁ ሰዎች ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን እና የሚያጠፉትን የስክሪን ጊዜ የሚገድብ፣ እንዲሁም የወላጅ ቁጥጥር የሚደረግበት አሰራር እንዲዘጋጅ ያስገድዳል። እድሜያቸው 15 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ታዳጊዎች ደግሞ የራሳቸውን አካውንት መክፈት ይችላሉ።
ህጉ በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ በቪዲዮ ማጋሪያዎች፣ በኦንላይን ጨዋታዎች እና በኤአይ (AI) ቻትቦቶች ላይ የሚተገበር ቢሆንም፣ የትምህርት ማግኛ ገጾችን እና መሳሪያዎችን ግን አይጨምርም።
በተጨማሪም ፕላትፎርሞቹ የተጠቃሚዎችን ትክክለኛ እድሜ የሚያረጋግጡበት የዲጂታል አሰራር እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ሲሆን፣ ህጉን በበላይነት ለመቆጣጠርም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የቁጥጥር ክፍያ የሚከፍሉበት አሰራር ይዘረጋል ሲል ፖለቲኮ ዘግቧል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: