Search

አፍሪካን የሚያነቃው የኢትዮጵያ ዲጂታል አብዮት

ረቡዕ ኅዳር 16, 2019 34

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት እያከናወነች ያለችው የዲጂታል ሽግግር፣ ሀገራችንን በቀጥታ ወደ አምስተኛው የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ አብዮት እያሸጋገራት ይገኛል።

ኢትዮጵያ ንጹሕ የኃይል አቅርቦትን፣ ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማቶችን፣ የሰው ኃይል ልማትን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (AI) በአንድ ወጥ የመደመር መዋቅር ውስጥ አስተሳስራለች።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ግዙፍ የመረጃ ማዕከላት ያለ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊታሰቡ አይችሉም።

ኢትዮጵያ ይህንን ቀድማ በመገንዘብ 98 በመቶ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይሏን ከታዳሽ ምንጮች በማመንጨት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና መሠረትነት ከ6 ጊጋ ዋት በላይ ኃይል ለነገው የኮምፒውቲንግ አቅም አዘጋጅታለች።

በ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ኢኒሼቲቭ ተጀምሮ ወደ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” እየተሸጋገረ ያለው ጉዞ በአኃዝ የሚለካ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።

በዚህም የቴሌኮም ተጠቃሚዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ አድጎ ከ91 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከ54 ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ ዜጎች በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸው ለዘመናዊ ፋይናንስና ሕዝባዊ አገልግሎት የጀርባ አጥንት ሆኗል።

የመሶብ አንድ ማዕከል ከ200 በላይ የመንግሥት ተቋማትን በአንድ ቋት ሲያስተሳስር፣ በጤናው ዘርፍ ደግሞ 3 ሺህ 800 ተቋማት በሄልዝኔት ተገናኝተው ከ200 በላይ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ከወረቀት ፋይል ወደ ኤሌክትሮኒክ የሕክምና መዝገብ ተሸጋግረዋል።

ኢትዮጵያ በአምስተኛው የቴክኖሎጂ አብዮት ውስጥ የውጭ ምርቶች ሸማች ብቻ ሆና ባለመቅረት፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የዓለም መነጋገሪያ ከመሆኑ በፊት በ2012 ዓ.ም በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ቀዳሚ መሆን ችላለች።

ኢትዮጵያውያን የጡት ካንሰርን፣ በስኳር ሕመም ሳቢያ የሚመጣ የዓይን ሕመምን እና የቆዳ በሽታዎችን አስቀድሞ የሚለዩ የAI ሞዴሎችን ሠርተዋል።

በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚግባባው “መላ” የተሰኘው የAI መድረክ፣ ቴክኖሎጂ ከሕዝቡ ባህልና ቋንቋ ጋር እንዲታረቅ አድርጓል።

የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ወደ ሰባት ሚሊዮን በሚያደርገው ጉዞ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት ማስታጠቁ እንዲሁም የAI ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ማፍለቂያ ማዕከላት በሀገር ውስጥ የጤናና የኢኮኖሚ መፍትሔዎችን የሚገነቡ ወጣቶችን ማፍራታቸው የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆም ነው።

ኢትዮጵያ “ተግባር ከቃላት በላይ ይናገራል” በሚል መርህ የገነባችው ይህ የተቀናጀ የዲጂታል ሥነ ምኅዳር፣ አፍሪካውያን ሀገራት የሌሎችን እርዳታ ሳይጠብቁ በራሳቸው አቅም፣ ኃይልና ዕውቀት ወደ አምስተኛው የቴክኖሎጂ አብዮት መዝለል እንደሚችሉ የሚያሳይ ሕያው ማሳያ ሆኗል።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: