የኢፌዴሪ መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሀገር ዐቅም የሚፈቅደውን ርምጃ እየወሰደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት የገጠሟትን የኢኮኖሚ ስብራቶች ለመጠገንና ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ግስጋሤ ለማፋጠን አዲስ የኢኮኖሚ ልማት ዕይታ እና መንገድ እየተከተለች ትገኛለች። በተያዘው ብዝኃ ዘርፍ፣ ብዝኃ ተዋናይ እና ብዝኃ ተጠቃሚ የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ፣ ለኢኮኖሚ ጥራትና አሳታፊነት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን በመሠረታዊነት ለመፍታት ልዩ ልዩ ሪፎርሞችን ጀምራ እያሳካች ትገኛለች፡፡ የእነዚህ ሪፎርሞች ዓላማ ሁለት ነው፡፡ በአንድ በኩል ነባር ሀገራዊ ስብራቶችን መጠገንና የተንከባለሉ ዕዳዎችን ማቃለል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዛሬንና የነገን ትውልድ ጥያቄዎች በመመለስ፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና በአስተማማኝ መሠረት ላይ መገንባት ነው፡፡
ሪፎርሙን በመተግበር በተገኙ ውጤቶችና ትሩፋቶች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ የቢዝነስ አንቀሳቃሾችና በግል ክፍለ ኢኮኖሚ የተሠማሩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የገቢ ሁኔታ ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን የቋሚ ደመወዝተኞች በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች ገቢ በተገቢው መጠን ሊጨምር አልቻለም፡፡ በአንድ በኩል በየጊዜው እየጨመረ በመጣው ሰፊ የመንግሥት ሠራተኛ ቁጥር ምክንያት የመንግሥት አጠቃላይ የደመወዝ ወጪ ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ለደመወዝ የሚያውለው ወጪ ከአጠቃላይ የመንግሥት ወጪ አንጻር ያለው ድርሻ ከ30 እስከ 32 በመቶ ይደርሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለእያንዳንዱ የመንግሥት ሠራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ በሚፈለገው መልክ መጨመር ባለመቻሉ አሁንም የሚከፈለው አነስተኛ ነው፡፡
ይሄንን በመረዳት እና በየጊዜው በመንግሥት ሠራተኛው በተለይም ዝቅተኛ ተከፋይ በሆነው ላይ እየደረሰ ያለውን የኑሮ ጫና ለማቃለል፣ በ2017 በጀት ዓመት 91 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ እንዲሻሻል ተደርጓል። ያለፈው የበጀት ዓመት እንደ ሀገር ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የገባንበትና በመንግሥት ወጪ ላይ ከፍተኛ ጫና የነበረበት ዓመት ቢሆንም፣ መንግሥት ባለው ቁርጠኛ ሰው ተኮር አቋም፣ የዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኛውን ደመወዝ ትርጉም ባለው ሁኔታ አሻሽሏል።
ደመወዝ ከመጨመር ባለፈ ቋሚ ገቢ ያለውን ሠራተኛ የመግዛት ዐቅም ለማሳደግ፣ መንግሥት ከ1994 ዓም ጀምሮ ሥራ ላይ በቆየው የቁርጥ ገቢ ግብር ዐዋጅ ውስጥ በተካተቱት የግብር ማስከፈያ ምጣኔ እና በተለያየ ደረጃ ግብር በሚጣልበት የገቢ ቅንፍ(income bracket) ላይ ማስተካከያ አድርጓል፡፡ በዚህም ሰፊ ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፣ በተለይም ከታክስ ነጻ የሆነውን የተቀጣሪ ገቢ ከብር 600 ወደ ብር 2000 ለማሳደግ ተችሏል።
መንግሥት ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን የመንግሥት ሠራተኛ ዝቅተኛ የክፍያ ሁኔታ እና ተያይዞ የመጣውን የኑሮ ጫና በአንድ ጊዜ በሚደረግ የደመወዝ ማሻሻያ ሊቀርፈው እንደማይችል ይገነዘባል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ከእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብልጽግና ምዕራፍ ሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ መሆን አለበት ብሎ ደግሞ ያምናል። ስለሆነም ከሚወሰዱ ሌሎች ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ ከመስከረም 2018 ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኛው ተጨማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መንግሥት ወስኗል፡፡
በዚህ ማሻሻያ፦
1. ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከብር 4760 ወደ ብር 6,ዐዐዐ እንዲያድግ ይደረጋል፡፡
2. ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከብር 21,492 ወደ ብር 39,000 እንዲያድግ ይደረጋል፡፡
3. የዲግሪ ተመራቂ መነሻ ደመወዝ ከብር 6,940 ወደ ብር 11,500 ይሻሻላል።
4. ከሲቪል ሰርቪስ ውጭ በተለያዩ ዘርፎች የተሠማሩ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝም ማሻሻያ ይደረግበታል፡፡
ይህ የደመወዝ ማስተካከያ ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ጠይቋል፡፡ ይሄም ለደመወዝ የሚወጣውን ጠቅላላ ዓመታዊ የመንግሥት ወጪ 56ዐ ቢሊዮን ብር ያደርሰዋል። ይህ የደመወዝ ጭማሪ ካለን የልማት ፍላጎት አንጻር አገልግሎቶችና መሠረተ ልማት ለማስፋፋት የሚያስፈልገንን ሀብት የሚሻማ ቢሆንም፣ የመንግሥት ሠራተኛውን ኑሮ ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ የተወሰነ ነው። ከዚህም ባሻገር የመንግሥት ሠራተኛው ችግር በደመወዝ ማሻሻያ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ በቀጣይ የቤት አቅርቦትን እና የጤና መድን ሽፋንን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሔዎች ይወሰዳሉ፡፡
መንግሥት ይሄንን የደመወዝ ማሻሻያ ሲያደርግ ጭማሪው በቂና የመጨረሻ ነው ብሎ በማመን አይደለም፡፡ በቀጣይነት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ማሻሻያው እየተተገበረ ሲሄድ ውጤትን መሠረት ያደረጉ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ፡፡ በተጨማሪም የጀመርነው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ይበልጥ ውጤት እያስመዘገበ በሄደ ቁጥር፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የትሩፋቱ ተቋዳሽ ይሆናል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በተገቢ ደረጃና መጠን ለመክፈል ከተፈለገ፣ ያንን የሚሸከም ሀገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ለአገልጋዮቿ ተገቢውን ክፍያ እንድትከፍል የሚያስችላትን ኢኮኖሚ የመገንባት ኃላፊነት ደግሞ፣ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ጭምር የተጣለ ብሔራዊ ግዴታ ነው፡፡ ካልተከልነው ዛፍ ፍሬ፣ ካልዘራነው ሰብል ምርት ልናገኝ አንችልምና፡፡ ኢኮኖሚያችን ካላደገ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ሊያድግ አይችልም፡፡ ለአብነት የታክስ ገቢያችንን በአንድ በመቶ ብናሳድግ እንኳን፣ ከ3ዐዐ ቢሊዮን በላይ ተጨማሪ ሀገራዊ ገቢ እናገኛለን፡፡ ይሄንን ለማሳካት ደግሞ በየመስኩ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ፡፡
በአጠቃላይ ዘላቂና ትርጉም ያለው የኑሮ ደረጃ መሻሻል እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ዓይናችንን ለአፍታም ቢሆን ከሀገራዊ ሕልማችን ሳንነቅል መረባረብ አለብን። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያውያን የሚከፍሉት የውዴታ መሥዋዕትነት አለ፡፡ ይህ መሥዋዕትነት ለነገ ሲባል የሚከፈል መሥዋዕትነት ነው፡፡ ለተሻለ ነገ ስንል የተወሰኑ ፍላጎቶቻችንን እንተዋለን፡፡
ውድ ዕውቀታችንን፣ ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን እንሠዋለን፡፡ ያደጉ ሀገራት ሁሉ የከፍታ ማማ ላይ የደረሱት በአንድ ወቅት መሥዋዕትነት በከፈሉ ትውልዶቻቸው ትከሻ ላይ ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በነጻነት የምንኖረው፣ ከመኖር ለሚበልጥ ሀገራዊና ሕዝባዊ ክብር ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን በሠው ዐርበኞቻችን ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች የድካማቸውን ያህል ክፍያ እንደማያገኙ ይታወቃል፡፡ ይሄም ለተሻለች ኢትዮጵያ እየተከፈለ ያለ መሥዋዕትነት እንደሆነ መንግሥት ዕውቅና ይሰጣል። ስለሆነም በዚሁ አጋጣሚ፣ በአነስተኛ ክፍያ ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ለሚገኙ አገልጋዮች መንግሥት ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
የመንግስት ሠራተኛው ያለውን የኑሮ ውድነት ተቋቁሞ ለመላው የንግዱ ማህበረሰብ ተገቢውን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብመንግስት ለሚወስዳቸው የሪፎርም እርምጃዎች አጋዥ እየሆነ መጥተዋል። ይሄው ተግባር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ይሁንናእንዳንድ የንግዱ ህብረተሰብ አካላት ከእዚህ ቀደም በተለምዶ የደመወዝ ጭማሪ ተደረገ በሚል በሸቀጦች ዋጋ ላይ እንደሚጨምሩ ይታወቃል፡፡በሰሞኑ በሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ አስታኮ እና ለኑሮ ውድነቱ መቋቋሚያ ተብሎ በተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ዜና በመስማት ህገወጥናምንም ምክንያት በሌለው መንገድ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ አድርገው በሚገኙት ላይ ደግሞ መንግሥት አስተማሪ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በቅድሚያ ያሳውቃል፡፡
በመጨረሻም ሕዝባችንን በንጽሕናና በትጋት በማገልገል፤ ከሚገባንና ከሚጠበቅብን በላይ በመሥራት፤ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመታገል፤ ከዕቅዶቻችን በላይ በማከናወን፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና እንደምናረጋግጥ መንግሥት ጽኑ እምነት አለው፡፡ የብልጽግና ጉዟችን በቀጠለ መጠን፣ በየምዕራፉ ሁላችንም የብልጽግናን ትሩፋት መቋደሳችን አይቀሬ ነው፡፡ ለዚያ ደግሞ ሁላችንም ወገባችንን አጥብቀንና ታጥቀን መትጋት አለብን፡፡ ይህ ሲሳካ ነጻነታችንን በደማቸው እንዳጎናጸፉን ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሁሉ፣ እኛም ሀገራቸውን ለማበልጸግ ዋጋ የከፈሉ ትውልዶች ተብለን ታሪክ ሲዘክረን ይኖራል።