Search

ያላትን ንብረት ሁሉ በመሸጥ የብዙዎች እናት የሆነችው አንያ ሪንግረን ሎቨን

እሑድ ነሐሴ 18, 2017 2405

አንያ ሪንግረን ሎቨን እ.አ.አ ሴፕቴምበር 4 ቀን 1978 ፍሬዴሪክሻቭን በምትባል በአንዲት ትንሽ የዴንማርክ የባህር ዳርቻ ከተማ ተወለደች

ገና በልጅነቷ እናቷን በሞት ያጣችው አንያ  የአልኮል ሱሰኛ ከሆነ አባት ጋር በማደጓ የልጅነት ዘመኗን ያሳለፈችው የወላጅ ፍቅርን ሳታጣጥም ነበር።

ይህ ሁኔታም ኋላ ላይ በወላጆቻቸው ችላ ለተባሉ ሕፃናት  እንድታዝን እንዳደረጋት ትናገራለች።

በዚህ ሁኔታ ያደገችው አንያ በአንዳንድ የናይጄሪያ አካባቢዎች በባእድ አምልኮ ምክንያት በወላጆቻቸው ስለሚጣሉ ሕፃናት የተሰራ ጥናታዊ ፊልምን እ.አ.አ. 2008 ላይ ትመለከታለች።

ይህ በቴሌቪዥን የተመለከተችው ፊልም የዴንማርካዊቷን ወጣት ይወት እስከመጨረሻ ለወጠው።

ከጥቂት ዓመታት በኋላም  ያላትን ንብረት እና ስራዋን በመተው ወደ ማላዊ በመጓዝ የበጎ አድራጎት ሥራን ጀመረች።

በማላዊ ቆይታዋም ባቋቋመችው ድርጅት አማካኝነት በማላዊ፣ ናይጄሪያ እና ሌሎች ሀገራት ወላጆች በባእድ አምልኮ ምክንያት ልጆቻቸውን መጣላቸው ተገቢ እንዳልሆነ የሚያስገነዘብ የንቃተ ሕሊና ማሳደግ  ሥራዎችን ስትሰራ ቆየች።

በኋላም በባእድ አምልኮ ትእዛዝ በገዛ ወላጆቻቸው ሜዳ ላይ የሚጣሉ ሕፃናትን ለመንከባከብ ወደ ናይጄሪያ ተጓዘች።

አንያ ወደ ናይጄሪያ አቅንታ ሳለ ብዙም ሳትቆይ አንድ ቀን በደቡባዊ ናይጄሪያ በምትገኝ ኡዮ በምትባል መንደር እየተጓዘች እያለ ልክ በዶክመንተሪ ፊልም አይታ እንደነበረው በባእድ አምልኮ ምክንያት በወላጆቹ የተጣለ የሁለት ዓመት ሕጻንን ተመለከተች።

ያኔ  ከመኪናዋ ወርዳ ወደጻኑ ተጠጋች።

ይህ ሕጻን በአጉል አምልኮ ምክንያት ለቤተሰቦቹ ጥሩ ዕድል አያመጣም በሚል እንዲጣል ተወስኖበት ለስምንት ወራት ያህል በሜዳ ተጥሎ ቆይቷል።

አንዳንድ ሰዎች በሚሰጡት ምግብ በሕይወት መቆየት ቢችልም አንያ በምታገኘው ወቅት ሰውነቱ በረሀብ ተጎድቶ በደንብ መንቀሳቀስ የማይችል ነበር። አንዳች ልብስ በሰውነቱ ላይ ያልነበረው ሕፃን በብርድ ክፉኛ ተጎድቶም ነበር።

በጎ አድራጊዋ አንያ ያየችው ነገር  በዶክመንተሪ ከተመለከተችው በላይ ሆነባት እና ለወራት ማንም ሊያስጠጋው ያልፈቀደውን የተጎዳ ሕፃጻን ቀርባ ውሃ ሰጠችው።

ወዲያውም እንደ እናት አቅፋ በመኪናዋ ውስጥ አስገብታ ወደ ቤቷ ይዛው ሄደች።

አንያ ሪንግረን ለታዳጊው ተስፋ ስትል ስም አወጣችለት። ብዙም ሳትቆይ በዚህ መጀመሪያ በታደገችው ሕፃን ስም የተስፋ ምድር የተሰኘ  የሕፃናት ማሳደጊያን ከፍታ ልክ እንደእርሱ በወላጆቻቸው የተተዉ ፤ ከቤት አውጥተው የተጣሉ  ሕፃናትን እየፈለገች ማሳደግ፣ መንከባከብ እና ማስተማር ጀመረች።

ለዚህ በጎ ተግባሯ ከተለያዩ ሀገራት እና ድርጅቶች እውቅና እና ሽልማት ያገኘች ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል እ.አ.አ በ2016 ቺልድረን ታውን የሚባለው ተቋም የሚሰጠውን የዓመቱ በጎ ፈቃደኛ ሽልማትየፖል ሀሪስ ፊሎው” ሜዳልያ አግኝታለኝ።

2019 በአፍሪካ ደረጃ ማኀበራዊ ሚዲያን ለማኀበረሰብ ግልጋሎት ላዋሉ ሰዎች የሚሰጠውን ሽልማት 2020 የናይጄሪያ የበጎ አድራጎት  ሽልማትን፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የኦድ ፌሎው ሽልማት  እን 2021 የዩኒቨርሳል ፖስ ፌዴሬሽን አምባሳደር በመሆን ተሹማለች።

በዚያው ዓመት የሂውማኒቲ ኢምፓክት ሽልማት፤ የላርስ ኤሪክ ፋውንዴሽን ከቦኤል ፋውንዴሽን የክብር ሽልማት ተሰጥቷታል

2023 የቀይ መስቀል የሰብዓዊ መብቶች ሽልማትን፤ በዴንማርክ ንጉስ ፍሬድሪክ ስም የተሰየመ የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝታለች

አንያ ሪንግረን በአሁኑ ወቅት መጀመሪያ ከጎዳና ላይ ያነሳችውን ተስፋን ጨምሮ ከመቶ በላይ በወላጆጃቸው የተተዉ ሕጻናትን እያስተማረች እና እየተንከባከበች ትገኛለች።

 በትዳር ሕይወቷም እዚያው ናይጄሪያ ውስጥ ከተዋወቀችው የሕግ ባለሙያ ባለቤቷ ጋር በትዳር የምትኖር ሲሆን አንድ ልጅም ወልጀዋል።

በአንድ ወቅት እጅግ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ለወራት ሜዳ ላይ ተጥሎ የተገኘው "ተስፋ" አሁን ላይ 12 ዓመት ታዳጊ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ተጥለው ከተገኙ ልጆች ጋር በሚኖሩበት "የተስፋ ምድር " በተሰኘው የሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ እየተማረ ይገኛል።

አንያ ያላትን ንብረት ሁሉ በመሸጥ ያስፋፋችውን የበጎ አድራጎት ሥራ በማጠናከር በርካቶችን እያሳደገችም ይገኛል።

 

 

በዋሲሁን ተስፋዬ