በሙቀት ሕግ መሰረት 1600 ዲግሪ ሴልሽየስ ማለት መስታወት እና ብረት ማቅለጥ የሚችል ከፍተኛ የሙቀት ኃይል ነው።
ይህ ብቻ አይደለም እንደ አልሙኒየም እና ሊድ የመሳሰሉ የብረት አይነቶችን እንደሰም ማቅለጥም ይችላል።
የዛሬ ሰማንያ ዓመት በጃፓኗ ሄሮሽማ ላይ የተጣለው ቦምብ ባረፈበት ቦታ ላይ የፈጠረው የሙቀት መጠን ግን ከዚህም በላይ ነበር።
በዕለቱ የተጣለው ቦምብ በአየር ላይ እያለ ሲፈነዳ 7000 ዲግሪ ሴልሼየስ የሙቀት መጠን የነበረው ሲሆን መሬት ላይ ሲያርፍ የፈጠረው ፍንዳታ ደግሞ የሙቀት መጠኑን ወደ 10 ሺህ ዲግሪ ሴልሺየስ አንሮታል።
በዚህ ሙቀት የአስፓልት መንገዶች ቀልጠዋል። በዚህ ቅጽበት ዕድለኛ የሆኑ ቢተርፉም ባይተርፉም ቆዳቸው በላያቸው ላይ ተንጠልጥሎ ከስቃይ ለመዳን በመፈለጋቸው እራሳቸውን ወደወንዝ እንዲወረውሩ ሆነዋል።
ከሞቴ አሟሟቴ እንዲሉ ለሟችም ለቋሚም ያልተመቸ አሟሟት በቅጽበት ውስጥ ሲከናወን ምንአልባት በክስተቱ በተዓምር የተረፉ እንኳ ምን እንደተከናወነ ማስታወስ አልቻሉም።
ይህ የኒውክሌር ቦምብ የፈጠረው ከፍተኛ ብረት አቅላጭ ሙቀት ሺዎች ለአይን ጥቅሻ በማትሆን ቅጽበት ሕይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል።
የሰዎች ሕይወት በሚዘገንን ሁኔታ እንዴት እንዳለፈ ያመላከተው ደግሞ ቦንቡ በወደቀበት 5 መቶ ሜትር ርቀት ላይ የነበሩ ከመዳብ የተሰራ የቡድሃ ምስል፣ መስታወቶች እና የቤት ጣሪያዎች እንደሻማ ቀልጠው የመገኘታቸው ጉዳይ ነው።
በእርግጥ ይህን የዓለም አሳፋሪ እና የሰው ልጆች የክፋት ጥግ ማሳያ የሆነ ድርጊት ከጃፓናውያን በስተቀር በአግባቡ የተማረበት ዳግምም አይፈጸም ብሎ አምርሮ የተጸየፈው ያለ አይመስልም።
ነሐሴ 6 ቀን 1945 ጃፓን በወቅቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚዋ ቢቀዛቀዝም በከተሞች አካባቢ የነበረው ሕይወት በተለመደው መልኩ ቀጥሎ ነበር።
በዚያን ዕለትም የሂሮሺማ ከተማ ነዋሪዎች ልክ እንደሌላው ቀን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አዋቂዎች ወደየሥራ መስካቸው መሰማራት ጀምረዋል።
ነገሮች ሁሉ ትላንት እንደነበረ ነገም ሊሆን እንደሚችለው አይነት መልክ ነው የነበረው።
ዓለም ጦርነት ውስጥ እንደነበረች ሀገራቸውም በአንደኛው ጎራ ተሰልፋ የድል ዜናዎችን ይሰሙ የነበሩት የሂሮሺማ ነዋሪዎች በሩቅ ይሰሙት የነበረው የጦርነት ድምጽ ሕይወታቸውን የሚፈትን ስለመሆኑ ግን አልጠረጠሩም።
ሆኖም ያ ዕለት እንደወትሮው ቀናት ሰላማዊና የተለመደ እንዳልሆነ የታወቀው ብዙም ሳይቆይ ነበር።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ጎራ ለይተው ሲዋጉ የነበሩት አሜሪካና ጃፓን ፀባቸው ተካሮ አሜሪካ የጃፓንን ከተሞች ለመምታት ወስና የጦር አውሮፕላኖቿን ወደጃፓን ላከች።
በሰማይ ላይ እየተምዘገዘጉ ወደጃፓን የአየር ክልል የተጓዙት የጦር አውሮፕላኖች የአንድን ከተማ ማንነት ገሀነም ሊያስመስሉ እንደሚችሉ እንኳን የማያውቁት አብራሪዎቹ እንደተለመደው ወታደራዊ ኢላማዎችን መትቶ የድል ዜናዎች ባለቤት መሆንን ነበር ያለሙት።
በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እልቂትን ያስከተሉት እና ምን ያህል ታላቅ ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ልዩ ቦምብ እንደያዙ አብራሪዎቹ ምንም መረጃ አልደረሳቸውም።
በዚህ መልኩ ወደጃፓን ግዛቶች ዘልቆ የገባው የአሜሪካ ቦምብ ጫኝ አውሮፕላን አሜሪካ ማንሃተን ፕሮጀክት በሚል ስም ለዓመታት በምስጢር ስታበለፅግ የቆየችውን እና ከምርምሩ ጊዜ አንስቶ በአጠቃላይ 1.89 ቢሊየን ዶላር መድባ የተሰራውን ግዙፍ ቦምብ በሂሮሺማ ሰማይ ላይ ቁልቁል ለቀቁት።
የተደገሰላቸውን አስከፊ አሟሟት የማያውቁት ነዋሪዎች በዚህ ቅጽበት ውስጥ እንኳ ነገሩን የሚረዱበት ስድስተኛ የስሜት ህዋስ አሊያም ሹክ የሚላቸው የምህረት ነፋስ አላገኙም።
በድል ጉጉት ወደመሬት የተወረወረው የኒውክሌር ቦንብ በረከት ይዞላት ይመጣ ይመስል በመሬት ስበት ይበልጥ እየተምዘገዘገ ምድር ላይ ለመድረስ 250 ሜትር ሲቀረው ፊውዞቹ ተቀጣጥለው አየር ላይ ሲፈነዳ የሂሮሽማ ሰማይ አንዳች የሞት ድግስ ውስጥ እንደገባች እና የሞት አፍ ላይ መሆኗን ምልክት አገኘች።
ግን ሁሉም ነገር የረፈደ ምልክት፤ መፍትሄ የሌለው ችግር ሆኖ ዐይን እያየ ወደሞት የመሄድ አስከፊ አሟሟት ነበር።
አሜሪካኖቹ ምን ያህል ጥፋት ሊያመጣ እንደሚችል እንኳ በውል የማያውቁት፣ ለሙከራ፣ የጥፋት ልኬቱንም የሃያልነት ማስመስከሪያ ይሆነናል ያሉትን "little Boy” የሚል ስም የሰጡትን ኑክሌር ቦምብ ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ብሩህ የነበረው ሰማይ ለሰከንዶች የፀሐይን ብርሃን በሚያስንቅ እሳታማ ብልጭታ ሞላው፤ የሂሮሺማ ምድርና ሰማይ በከባድ ጥቁር ሀምራዊና ግራጫ ጭስ ተሸፈነ።
በስበት ሕግ መሰረት ይጠቅማት ይመስል ስትጎትተው የነበረው ቦምብ ምድር ላይ ሲያርፍ መሸከም አቃታት፤ በተፈጠረው ሀይለኛ ፍንዳታና ቦምቡ በፈጠረው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰማንያ በመቶ የሚሆኑት የከተማዋ ህንጻዎች መፈራረስ ጀመሩ። የተፈጠረው ሀይለኛ ሙቀት ደግሞ በከተማዋ ውስጥ በተለያየ ቦታ እሳት አስነሳ።
ቦምቡ ባረፈበት አካባቢ የነበሩት ህንጻዎች ከመፈራረስም በላይ በቅፅበት ወደ አመድነት ተቀየሩ። ቆዳቸው በሰውነታቸው ላይ የተንጠለጠለ፣ ሰውነታቸው ከልብሳቸው ጋር የተጣበቀባቸው ሰዎች ዋይታና እሪታ ምድሪቱን ሞላት። የሰዎችን የዋይታ ድምጽ መስማት እራሱ በእዚህ ከባድ አውዳሚ ክስተት ውስጥ ብርቅ ሊሆን ይችላል።
78 ሺህ ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው አለፈ። የአብዛኛዎቹ አስከሬን ማግኘት አልተቻለም። ብዙዎች የተቃጠለ ሰውነታቸውን ለማብረድ ራሳቸውን ወደወንዝ እየወረወሩ ለሞት ተዳረጉ።
በአደጋው ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከ140 ሺህ በላይ ደረሰ። በዚህ በኑክሌር ቦምብ የተፈጠረውን ከ7 ሺህ 200 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ ሙቀት እንኳን የሰው ልጅ እና እንስሳት ብረትን ማቅለጥ የሚችል ነበረና ከአደጋው በኋላ በየቦታው የቀለጡ የቤት ጣራዎች፣ ቅርጻቸው የተለወጠ መስታወቶች፣ ሙቀቱን መቋቋም አቅቷቸው የሟሙ የአልሙኒየም ዕቃዎች ተገኝተዋል።
ቦምቡ ከወደቀበት ቦታ በ500 ሜትር ርቀት ላይ የነበረው የዞንጂ ቤተ-መቅደስ ከነሀስ የተሰራ የቡድሃ ምስል በከፊል ቀልጦ ተገኝቷል። እነዚህ በሀይለኛው ሙቀት ምክንያት ቀልጠው የተጣበቁ፣ ቅርጻቸውን የለወጡ ሳንቲሞች፣ መስታወቶች እና የቡድሃ ማስታወሻዎች አሁን ድረስ ሂሮሺማ በሚገኘው የመታሰቢያ የሰላም ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ።
በድል ዜና ውስጥ የነበረችው አሜሪካ በደረሰው ውድመት ያዘነች አይመስልም። ይልቁንም ዓለም በሙሉ ብቸኛ ገዥነቷን እና የበላይነቷን አሁንም በሚገባ ጠንቅቆ እንዲያውቅ ይህን የጥፋት ቦምብ መድሃኒት ሆኖ ተሰምቷቷል። ሂሮሽማ ላይ የደረሰውን ውድመት የተመለከቱ ቦምቡን የጣሉ የጦር ጀት አብራሪዎች እንኳ ሰዎኛ ስሜታቸው ገዝፎባቸዋል።
ቀድሞም ቢሆን ምን ጭነው እንደሄዱ እና ምን እንደጣሉ ያላወቁት አብራሪዎች ነገሩ ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁት እና አስፈሪ እንደሆነ ከአየር ላይ ብቻ ተመልክተው በጥልቅ የሃዘን ስሜት ውስጥ ገብተዋል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት ግን ሰዎችን እንደሰው አሳዘነ እንጂ የወቅቱ የአሜሪካ ጦር የደረሰበትን ደረጃ ከማመላከት በላይ ሰዎኛው ስሜት የጠፋባቸው የጦር ነጋሪት መችዎች በሦስተኛው ቀን በነሐሴ 9 ሊደግሙት ቀጠሮ ይዘዋል።
በሂሮሽማ የደረሰው ውድመት እና ዘግናኝ ድርጊት እንኳን ለዓለም ቀርቶ ለጃፓናውያን እንኳ ዜናው ተሰምቶ አላለቀም። አሜሪካ “Fat man” የተሰኘውን ሁለተኛውን የአቶሚክ ቦምብ በጃፓኗ ናጋሳኪ ከተማ ላይ ጣለች። አሁን ዓለም ነገሩን በድፍን ቢሰማውም ጃፓን ግን የወረደባት መዓት በቃላት የሚገለጽ አይደለም።
በታሪኳ አይታ የማታውቀው ውድመትን በዜጎቿም በሃብቶቿም ላይ የወረደባት ጃፓን ከሂሮሽማው አሰቃቂ ህመሟ ሳታገግም የሞቱ ዜጎቿን ሳትቀብር ምን እንደተፈጠረ እንኳን በአግባቡ ሳትረዳው ሌላ ዘግናኝ ጥቃት ደረሰባት።
በናጋሳኪው ሌላ የኑክሌር ውድመት በቅፅበት 27 ሺህ ሰዎች ለሞት ተዳረጉ። ከቀናት በኋላም የሟቾች ቁጥር ሰባ ሺህ ደረሰ።
ጃፓን በሁለቱ ከተሞች በደረሰባት የኑክሌር ጥቃት በቀጥታ በዕለቱ የሞቱትንና በዚህ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈውን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎቿን አጣች።
ከዚህ አደጋ ለጊዜው የተረፉ ሰዎችም በኑክሌር ቦምብ ምክንያት በተፈጠረው ጨረር ቀስ በቀስ ፀጉራቸው መርገፍ ጀምሮ ለተለያዩ ህመሞች ተጋልጠው ህይወታቸውን በስቃይ አሳልፈዋል።
በዚያ ስፍራ ለዓመታት ጤናማ የነበረው የሕይወት ዑደት ተቀይሮ እስከ ብዙ ዓመታት የኒውክሌር ጦስ የእናቶች ፅንስን እስከመመረዝ ደርሷል።
ዛሬም ድረስ ዓለም ከኒውክሌር ጦር መሳሪያ የጸዳች ትሆን ዘንድ ከልባቸው የሚማጸኑት ጃፓናውያን መከራውን በሞት ብቻ ሳይሆን በሕይወትም አይተውት ስለኖሩት ነው። በእርግጥ የሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ውድመት በኋላ የኒውክሌር ቦምብ አስከፊነትን የተረዱ ሃያላኑ ሀገራት ተሰባስበው ከዚህ በኋላ ከእኛ እጅ እንዳይወጣ ብለው ቃልኪዳን አስረዋል። እነዚህ እኛ ብቻ ይዘን እንቅር ሌሎች መያዝ የለባቸውም ብለው የተስማሙበት ቃል ኪዳን የዓለም ህግ ሆኖ የሌሎች ሀገራት መቅጫም ሆኖ እያገለገለ ነው።
ሰሞኑን ተካሂዶ በነበረው የሰማንያኛ ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም ላይ የሂሮሽማ ከንቲባ ሂድሂኮ ዩዛኪ ሲናገሩ “እስካሁንም ድረስ በተለይ እንደ ኒኖሽማ አይስላንድ ባሉ አካባቢዎችና በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ሁለት ጫማ ያህል ወደታች ከቆፈርክ የሰው አፅም ልታገኝ ትችላለህ፤ አሁን የምንኖረው በዚያ ላይ ነው” ሲሉ የቦምቡን ጥቁር ጠባሳ ተናግረዋል።
ዛሬ በዓለም ላይ 13 ሺህ የሚሆኑ ከዚህም በላይ እልቂት ማድረስ የሚችሉ የአቶሚክ መሳሪያዎች በተለያዩ ሀገራት እጅ ይገኛሉ። እነዚህ ቦምቦች የማውደም እና እልቂት የመፍጠር መጠን በሂሮሽማና ናጋሳኪ ላይ ከተጣሉት 3 ሺህ ጊዜ በላይ የሚበልጥ ሀይል ያላቸው ናቸው።
ይህን በመረዳት ጃፓን በራሷ የደረሰው በሌላ እንዳይደርስ የሰላምን አስፈላጊነት ከልቧ የምትሰብክ ሀገር ሆናለች። እንደጃፓን ሁሉ የኒውክሌር ቦምብ አስከፊነትን ደርሶባቸው ያላዩ ሀገራት ዛሬም ከኔውክሌር የጸዳ ዓለም እንፍጠር ቢሉም በጓዳቸው ግን ግዙፍ የኔውክሌር ማብላያ ጣቢያዎችን ከፍተው “ኒውክሌርን ለሰላማዊ የሃይል ምንጭ” የሚል የዳቦ ስም ሰጥተው ነው የሚገኙት።
በምድርም ላይ ሆነ ከምድር በታች ድብቅ ቦታዎችን ለኔውክሌር ማበልጸጊያነት የሚውል የማብላያ ጣቢያዎችን እጅግ ውድ በሆነ ወጭ የሚያካሂዱት ሀገራት አንዳንዴ የኒውክሌር ቦምብ መታጠቃቸውን በይፋ ሲነግሩን አንዴም፣ ሁለቴም ሦስቴም ጭምር ነው።
በጃፓን ላይ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ዘግናኝ የሆነውን የጥፋት ተልዕኮ የተመለከቱም ሆነ በታሪክ ያዩ የዓለም መሪዎች ዛሬ ልክ እንደጃፓን ሁሉ ይህን ጥፋት ዳግም ላለመድገም ከልባቸው ቃል የገቡ አይመስልም። በእርግጥ በቃል የሚነገሩ በተግባር የማይገለጡ ብዙ ሥራዎች በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ነው። ዓለም ዳግም ከእንዲህ ያለው ጥፋት ራሷን ታርቃለች ወይ የሚለው የሰው ልጆች ሁሉ ፍላጎት ቢሆንም ፍላጎት እና ተግባር ግን የተገናኙ አይመስልም።