የአፋብን ወታደራዊ አዛዥ ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከነአጃቢዎቹ ላሊበላና አካባቢው ወደ ሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት በሰላም ገብቷል።
ኮማንዶ ፍቅሩ ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ የወሰነው የትግል ሂደቱ የአማራን ሕዝብና ሀገርን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን በመገንዘቡ እንደሆነ ገልጿል።
አላማችን በውስጣችን ባሉ አድርባዮች፣ በህወሓት እና በውጭ ኃይሎች ተጠልፏል ያለው ኮማንዶ ፍቅሩ፣ የታሪክ አተላ ተሳታፊና የሌሎች ፍላጎት አስፈጻሚ መሆን ስላልፈለገ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሱን በዝርዝር አስረድቷል።
ማንኛውም ችግር በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት እንዳለበት እምነቱን የገለጸው አመራሩ፣ ባልሰከነ ግንዛቤ ተገፋፍቶ ሕዝብንና ሀገርን መበደሉ ከፍተኛ ፀጸት እንደፈጠረበትም ተናግሯል።
ካለፈው ስህተቱ ተምሮ ሕዝቡንና ሀገሩን ለመካስ መዘጋጀቱን ያረጋገጠው ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ፣ በአሁኑ ወቅት በጫካ የሚገኙ ሌሎች አባላትም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረቡን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡