የኢንፎርሚሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 5ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ የሰለጠኑ 1140 ተማሪዎች አስመርቋል።
ሀገር አቀፍ የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ በኢትዮጵያ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ደኅንነት ፍላጎት ለመመለስ፣ ወጣት ባለሙያዎችን እና ተማሪዎችን ለማፍራት እንዲሁም ተግባራዊ የችግር አፈታት ክህሎትን ለማሳደግ ያለመ የውድድር እና የክረምት ስልጠና መድረክ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ይዞት የሚመጣውን ዕድልና ስጋት ለይቶ መጠቀም የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል።
የተሰጠው ሥልጠናም የማነሳሻ እንጂ የቴክኖሎጂው ዕውቀትና ክህሎት የሚያልቅ እንዳልሆነ ያመዘገቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሉ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ብቁ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ለምትሰጠው የዲጂታል አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።
ተሳታፊዎች በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባራዊ ሁኔታዎች ፈጣን ውሳኔ እንዲሰጡና ችግሮችን እንዲፈቱ የሚያስችሉ ውስብስብ የሳይበር ጥቃት ሁኔታዎችን እንዲመረምሩና የመከላከያ መፍትሔዎችን እንዲያመነጩ የሚያግዙ ስልጠናዎች እንዳገኙ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር በአቶ ቢሻው በየነ ገልጸዋል።
የኢንፎርሚሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትግስት ሀሚድ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ ለምትሻው ቴክኖሎጂ ብቁ የሰው ኃይል አስፈላጊ በመሆኑ መዘጋጀቱን ገልጸው ተመራቂዎች ያገኙትን ሥልጠና በመጠቀም የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል በተግባር ውጤታማ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ለሚሰጡ የዲጅታል አገልግሎቶች ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጡም በዘርፉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ተመራቂዎቹም በክረምቱ የአንድ ወር ቆይታቸው ከአሠልጣኞችና በዘርፉ ካሉ ተቋማት የሳይበር ደኅንነት እና የተለያዩ ልምዶች ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ዘመናዊ የሳይበር ስጋቶች ፈጣንና ውስብስብ በመሆናቸው፣ ድንገተኛ ጥቃቶችን በፍጥነት መቋቋም የሚችል ዝግጁ የሰው ኃይል ማፍራት ለሀገራዊ ደኅንነት ወሳኝ በመሆኑ ይህ መርሐ ግብር ለሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት አቅም ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተጠቅሷል ።
በዋለልኝ ታምር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: