ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትና የልማት ጉዞ የሚለካው በገንዘብና በተፈጥሮ ሀብቶቿ ብቻ ሳይሆን በእጇ ላይ ባለው ጥራት ያለው መረጃም ጭምር ነው። መረጃ የውሳኔ መሠረት፣ የምርምር ግብዓትና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ዋነኛ ግብዓት በመሆኑ በአግባቡ መሰብሰቡ፣ መተንተኑና ጥቅም ላይ መዋሉ ለሀገራዊ ልማት ወሳኝ ነው።
በዘመናዊው ዓለም መረጃ ከነዳጅ ጋር የሚነጻጸር ውድ ሀብት ቢሆንም እውነተኛ ዋጋው የሚጎላው በብዛቱ ብቻ ሳይሆን በጥራቱና ለተፈለገው ዓላማ በሚውልበት መንገድ ነው። በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የዳታ ትንተና ቴክኖሎጂዎች እየተስፋፉ በመጡበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ፣ ታማኝና ወቅታዊ መረጃ ማግኘት ለውጤታማ ውሳኔ አሰጣጥ የማይተካ ሚና አለው።
በኢትዮጵያ የመረጃ አሰባሰብ ሂደት ከዚህ ቀደም በወረቀት ቅጾች ላይ ተመስርቶ ይከናወን የነበረ በመሆኑ በርካታ ማነቆዎች ነበሩበት። መረጃን በእጅ መሰብሰብ፣ ወደ ኮምፒውተር ማስተላለፍና ለትንተና ማዘጋጀት ተጨማሪ ጊዜና ከፍተኛ ወጪ ከመጠየቁ ባሻገር ለስህተት የተጋለጠ ነበር።
በተጨማሪም መረጃዎችን በውጭ ሀገራት ሰርቨሮች ላይ ማከማቸት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከመጨመሩም በላይ፣ የሀገር መረጃ በተለያዩ ሀገራት ተጽዕኖ ሥር እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል።
ይህን መሠረታዊ ክፍተት ለመሙላት በሀገር ውስጥ የተገነባው "ዳታ ፕላስ" የተሰኘው ዲጂታል መድረክ፣ የመረጃ አሰባሰብን፣ ማደራጀትን፣ ትንተናን እና ማቅረብን በአንድ ላይ ያቀናጀ ሀገራዊ መፍትሔ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ዳታ ፕላስ የመረጃ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። የመረጃ ሉዓላዊነት ማለት መረጃን በሀገር ውስጥ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገር ውስጥ ሶፍትዌርና ሰርቨር በመጠቀም በአግባቡ መሰብሰብ፣ ደህንነቱን መጠበቅና ለሀገራዊ ጥቅም ማዋል ነው።
ዳታ ፕላስ፣ ጥናትን ከመቅረጽ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የውሳኔ አሰጣጥ ያለውን ሙሉ ሂደት ያቀናጃል። ሥርዓቱ ተደጋጋሚ ምላሾችን የመለየትና የመከለስ አቅም ስላለው፣ የመረጃን ጥራት በተደራጀ ሁኔታ ያረጋግጣል። ይህም ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለመንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ ለንግድ ድርጅቶችና ለተመራማሪዎች አስተማማኝ የምርምርና የፖሊሲ ማሻሻያ ግብዓት ያቀርባል።
በአጠቃላይ፣ በሀገር ውስጥ የተገነባ የመረጃ መድረክ መጠቀም የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ ባለፈ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አቅምን ያሳድጋል፤ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችንም ይፈጥራል። በቀጣይ መድረኩን በሀገራዊ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ገበያ ለማስፋፋት የተያዘው ዕቅድ ኢትዮጵያን በዘርፉ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት ነው።
የመረጃ ሀብትን በአግባቡ መሰብሰብና መጠበቅ ለሀገራዊ ዕድገትና ለወደፊት የዲጂታል ስኬታችን መሠረት ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: