የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዕድገት ምህዳር በቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ እና በዕውቀት መሪነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ወጣቱ ትውልድ አዲሲቷን እና የበለጸገችዋን ኢትዮጵያ ለመረከብ አርቆ አሳቢነትን፣ የቴክኖሎጂ ክህሎትን እና ሀገራዊ አደራን አስተባብሮ መያዝ ይኖርበታል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለወጣቶች ምቹ የፈጠራ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሥራ ዕድል ምህዳርን ለመፍጠር በዘርፉ ሰፊና ስትራቴጂያዊ መሠረተ ልማቶችን እየገነባች ትገኛለች።
በዚህም የያዘችውን "ዲጂታል ኢትዮጵያ" ስትራቴጂያዊ ግብ ለማሳካት የተገነቡት የሳይንስ ሙዚየም፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከላት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ፓርኮች ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ የዕውቀት፣ የችግር ፈቺነት እና የፈጠራ ማዕከል ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።
እነዚህ ዘመናዊ ተቋማት ወጣቶች እና አዳጊዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ፣ የዳታ ሳይንስ እና የሳይበር ደኅንነት ምህዳርን በአካል ተገኝተው እንዲመረምሩ እና የተደበቀ አቅማቸውን ወደ ተግባራዊ የፈጠራ ሥራ እንዲቀይሩ ሰፊ መንገድ ከፍተዋል።
በተጨማሪም የፈጠራ ማዕከላቱ ወጣት ስታርት አፖች አዳዲስ የቢዝነስ ሀሳቦቻቸውን ወደ ገበያ መቀየር እንዲችሉ የፋይናንስ፣ የካፒታል እና የቴክኒክ ድጋፍ የሚያገኙበት ምቹ የኢኮኖሚ ምህዳር ፈጥረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ለወጣቶች የፈጠራ ሀሳብ ምቹ፣ ድጋፍ ሰጪ እና የወደፊት ተስፋን የምታበስር ሀገር እየሆነች መምጣቷን በተግባር የሚያስረግጥ ነው።
ወጣቱ ትውልድ የሀገር ውስጥ ችግሮችን በሀገር በቀል የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች ከመፍታት ባለፈ፣ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ በመውጣት በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በሎጂስቲክስ እና በፋይናንስ ዘርፎች የሚታዩ አገልግሎቶችን ማፋጠንና ክፍተቶችን በዲጂታል አማራጮች መደገፍ ይጠበቅበታል።
የሳይንስ ሙዚየም እና ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ማዕከላት መገንባት ኢትዮጵያ በወጣቱ ትውልድ ብቃትና በመፃኢ ዘመኗ ብሩህነት ላይ የጣለችውን ትልቅ እምነት ያሳያሉ።
ስለሆነም ወጣቱ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ወቅቱ የሚጠይቀውን የክህሎት፣ የፈጠራ እና የአርቆ አሳቢነት ደረጃ በመጨበጥ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የከፍታና የብልጽግና ምዕራፍ የማሸጋገር ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: