Search

የቤጂንግ ሚሳኤል ትርዒት:- ቻይና ኃያልነቷን ለአሜሪካ የላከችበት ጥበብ

ዓርብ ነሐሴ 30, 2017 1930

ቻይና የላቁ የሌዘር መሳሪያዎችን እና አዳዲስ ሚሳኤሎችን አሳይታለች። እነዚህስ አሜሪካን የሚያስፈሩት ለምንድን ነው?

 

ረቡዕ ዕለት ቻይና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን እና በጃፓን ላይ የተቀዳጀችውን ድል 80ኛዓመት ለማክበር ወታደራዊ ሰልፍ አካሒዳለች።

 

በቤጂንግ ታላቁ አደባባይ የተደረገው ይህ ዝግጅት፣ ቻይና በቅርብ ጊዜ ከተከሰቱ ወታደራዊ ግጭቶች የተማረችውን ትምህርት በመጠቀም ያፈራቻቸውን የላቁ የጦር መሳሪያዎች አሳይታበታለች።

 

 

በሞስኮ የብሔራዊ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የኮምፕሪሄንሲቭ የአውሮፓ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል ዳይሬክተር ቫሲሊ ካሺን፣ ቻይና በየዓመቱ ወታደራዊ ሰልፍ የማታደርግ በመሆኑ የዚህ ሳምንት ዝግጅት ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።

 

“ይህ ሰልፍ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ከነበሩት የቻይና ሰልፎች ፈጽሞ የተለየ ነው። አዲስ ወታደራዊ ጥንካሬ ለማሳየት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን በቻይና የጦርነት ዶክትሪን ሰነዶች ላይ ለውጦችን ሊያመለክት ይችላል” ብለዋል።

 

በሰልፉ ላይ የታዩት አዳዲስ ታንኮች፣ የሌዘር መሳሪያዎች እና ሚሳኤሎች ከአሜሪካ ጋር በሚፈጠር ግጭት ውስጥ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ስለመሆናቸው ጠቋሚ ናቸው።

 

ምንም እንኳን ለሰልፉ የሚደረገው ልምምድ ከፍተኛ ትኩረት ቢያገኝም፣ የቻይና ወታደራዊ ኃይል የውጭ ታዛቢዎችን ማስደነቅ ችሏል። DF-61 አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን (ICBMs) የያዙTransporter erector launchers (TEL) ለመጀመሪያ ጊዜ በወታደራዊ ሰልፉ ላይ ታይተዋል።

 

ባለ ስምንት-አክስል ቻሲስ ላይ የተገጠመው የዚህ ስርዓት ዝርዝር መረጃ ግን አልተገለጸም። DF-61 ከሩሲያ Yars TEL ጋር በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፣ ሚሳኤሉን በደቂቃዎች ውስጥ ከየትኛውም የጥበቃ መስመር ላይ ማስወንጨፍ መቻሉ ልዩ ያደርገዋል። DF-61 በአውሮፓውያኑ 2019 ሰልፍ ላይ ከታየው DF-41 TEL የተሻሻለ ሊሆን እንደሚችል ባለሞያዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 

 

DF-41 ከ12,000 እስከ 15,000 ኪሎሜትር የሚደርስ ርቀት የሚሸፍን እና እስከ አስር የሚደርሱ የኒውክለር አረሮችን መሸከም እንደሚችልም ይታመናል።

 

በተጨማሪም አዲስ የDF-31 ICBM ዓይነት፣ DF-31BJ የተባለው፣ በቤጂንግ ታይቷል። የDF-31A ዓይነት ከ13,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት እንዳለው ይታወቃል። እናም ይሄኛው ከቀደሙቱ ሊልቅ እንደሚችል መገመት አያዳግትም::

 

ሰልፉ የJL-3 አህጉር አቋራጭ ሰርጓጅ-ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳኤልንም አሳይቷል። የType 094 “Jin” ክፍል የስትራቴጂክ የኑክሌር ሰርጓጅ መርከቦች እስከ 12 የሚደርሱ እንደነዚህ ያሉ ሚሳኤሎችን መሸከም ይችላሉ።

 

ብራንደን ጄ. ዌይቸርት በ“The National Interest” መፅሔት ላይ እንደጻፈው፣ ይህ አዲስ ሚሳኤል ቻይና ከአደጋ ነጻ ከሆኑ የባህር ዳርቻ ውሃ ላይ ሆነው አሜሪካን መምታት ያስችላቸዋል።

 

ዌይቸርት “በአህጉር አቋራጭ ርቀቱ እና በርካታ የኒውክለር አረሮችን የመሸከም አቅሙ፣ JL-3 በኢንዶ-ፓሲፊክ ውስጥ ያለው ወታደራዊ የኃይል ሚዛን ወደ ቻይና እየተሸጋገረ ባለበት ወቅት ቻይና ለአሜሪካ እና ለአጋሮቿ አስፈሪ ተፎካካሪ እንድትሆን ያደርጋታል” ሲሉ ጽፈዋል።

 

ቤጂንግ የDF-5 ICBM አዲስ ዓይነት የሆነውን DF-5C አሳይታለች። በሰልፉ ላይ እንደተገለጸው፣ ሚሳኤሉ ዓለም አቀፍ ሽፋን አለው። ይህ ማለት ምናልባትም በምህዋር የሚሽከረከር የጦር ራስ የተገጠመለት ሊሆን ይችላል።

 

የመጀመሪያው ጠጣር ናፍጣ የሚጠቀም DF-5 በአውሮፓውያኑ 1971 አገልግሎት የገባ ሲሆን፣ የተሻሻለው DF-5B ደግሞ የ5,000 ኪሎ ግራም የመሸከም አቅም ያለው ከመሆኑም በላይ የተለመዱ የአየር መከላከያ ስርዓቶችን ማለፍ የሚያስችሉ የላቁ ቴክኖሎጂዎች አሉት።

 

እንደ ዘገባዎች ከሆነ ሚሳኤሉ በ2017 ተሞክሯል። እስከ 12 የሚደርሱ መርከቦችን በገለልተኛነት ኢላማ ማድረግ የሚችል (MIRV) ስርዓት እንዳለው ይታመናል።

 

ከሩሲያ Kinzhal ሚሳኤል ጋር የሚመሳሰል አዲስ የJL-1 አየር-ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችም በቤጂንግ ታይተዋል። በገለጻው መሰረት፣ እነዚህ ከሩሲያ Kinzhal ሚሳኤሎች ጋር የሚመሳሰሉት አውሮፕላኑ ወደተወሰነ ከፍታ እና ፍጥነት ከደረሰ በኋላ ይወነጨፋሉ።

 

በተጨማሪም፣ CJ-1000 ሃይፐርሶኒክ ረጅም ርቀት የሚጓዝ የክሩዝ ሚሳኤል አስወንጫፊዎች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በሕዝብ ነጻነት ሠራዊት የባህር ኃይል አገልግሎት ላይ የሚውሉ YJ-18C ረጅም ርቀት የሚጓዙ የክሩዝ ሚሳኤሎች እና በቻይና አየር ኃይል የሚጠቀሙ CJ-20A ሚሳኤሎችም ለእይታ ቀርበዋል።

 

አዲስ ታንኮች እና የውጊያ ተሽከርካሪዎች በሰልፉ ልምምድ ወቅት ታዛቢዎች ተመልክተዋል:: ከእነዚህም ውስጥ አዲስ የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን ZTZ-201 ታንክን እና ታንክ ደጋፊ የውጊያ ተሽከርካሪዎች ናቸው ለዕይታ የቀረቡት። 

 

በሰልፉ አስተዋዋቂዎች መሰረት፣ ሁለቱም ተሽከርካሪዎች “Type 100” ተብለው ይመደባሉ።

 

እነዚህ ተሽከርካሪዎች ዘመናዊ ምላሽ ሰጪ ትጥቅ እና ራዳር እንዲሁም ኦፕቲካል ሴንሰሮችን ያካተተ ንቁ መከላከያ ስርዓት የተሻለ ጥበቃ ይሰጣል። ታንኩ ከ120 ሚሜ መድፍ ጋር ሊወዳደር እንደሚችል በሚታመነው ባለ 105 ሚሜ የጦር ግንብ የተገጠመለት ሲሆን፣ በሩቅ የሚሰራ የማሽን ሽጉጥም አለው።

 

የታንክ ደጋፊ የውጊያ ተሽከርካሪው አውቶማቲክ መድፍ ያለው ሲሆን፣ የስለላ ድሮን የተገጠመለትም ነው። በተሽከርካሪው የኋላ ክፍል የተቀመጡ ሁለት አብራሪዎች ድሮኑን መቆጣጠር ይችላሉ። አሽከርካሪዎቹም በአውግመንትድ ሪያሊቲ መነጽሮች የታጠቁ ናቸው።

 

የሌዘር ሚሳኤል መከላከያ ስርዓቶች የቻይና መከላከያ ኢንዱስትሪ ለአየር መከላከያ እና ለሚሳኤል መጥለፍ አገልግሎት የሚውሉ በርካታ የሌዘር ስርዓቶችን አዘጋጅቷል። በሰልፉ ላይ LY-1 የባህር ኃይል ሌዘር ስርዓቶች በዊልድ መድረኮች ላይ ታይተዋል። 

 

በተጨማሪም፣ በባለ አራት-አክስል የጭነት መኪና እና በባለ ሶስት-አክስል የታጠቀ ተሽከርካሪ ላይ የተገጠሙ ሁለት ሌሎች የሌዘር ስርዓቶች ታይተዋል። እነዚህ ምናልባትም ለመሬት ኃይሎች የተነደፉ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል።

 

አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገሮች በአሁኑ ጊዜ በሌዘር ላይ የተመሰረቱ የአየር መከላከያ ስርዓቶችን እያበለጸጉ ነው። እነዚህ ውድ በሆኑ ሚሳኤሎች ስጋቶችን ከመጥለፍ ይልቅ ወጪ ቆጣቢ አማራጭ ይሰጣሉ፣ በተለይ ዋጋቸው ዝቅተኛ የሆኑ የካሚካዜ ድሮኖች ስብስቦችን ለመከላከል የሚያስችሉም ናቸው።

 

ቻይና ያሳየቻቸው አዳዲስ ሚሳኤሎች እና የሌዘር መሣሪያዎች የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ወታደራዊ የበላይነት ለመፈታተን ያላትን የላቀ አቅም ያሳያሉ። የኒውክሌር አቅሟን በዓይነት እና በብዛት እያሰፋች ሲሆን፣ በተለይም አሜሪካን በቀጥታ ሊመቱ የሚችሉ ሚሳኤሎችን አሳይታለች። 

 

እነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች ቻይና የአሜሪካን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመቀነስ እና በዓለም ላይ ወታደራዊ ኃይሏን ለማስፋፋት እየሰራች መሆኑን ያመላክታሉ።

 

ወታደራዊ ሰልፉ ደግሞ የቻይና ጦር ከሩሲያ እና ከሌሎች የውጭ አቅራቢዎች በመመካት ይሰራ የነበረበት ጊዜ ማብቃቱንም ያመለክታል። 

 

የቻይና ወታደራዊ ምርምር እና ልማት አሁን በራሱ አቅም የላቁ የጦር መሳሪያዎችን መፍጠር መቻሉን ያሳያል። የሰልፉ ዋና መልእክት ለአሜሪካ እና አጋሮቿ የቻይናን ኃይል በማሳየት፣ በተለይ ታይዋንን በሚመለከት ግጭት ውስጥ ከመግባት በፊት ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ ማሳሰብ ነው።

 

ምንም እንኳን የቻይና ጦር በቴክኖሎጂው እየተሻሻለ ቢመጣም፣ ብዙዎቹ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎቹ በጦር ሜዳ ላይ እስካሁን አልተሞከሩም። በተቃራኒው የአሜሪካ ጦር በኢራቅ እና በዩክሬን ግጭቶች ውስጥ በጦር ሜዳ ላይ የተፈተነ ልምድ አለው። ሆኖም ግን ቻይና አዳዲስ እና የላቁ የጦር መሳሪያዎችን ማምረት እና ማሳየቷ የዓለምን የጦር ኃይል ሚዛን በመቀየር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ያመለክታል።

 

በሰለሞን ገዳ