በቻይናዋ ኩንሻን ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያን ቡና ያለምንም የሰው ልጅ እርዳታ በጥበብ የሚያፈላውን ሮቦት እና ላለፉት 8 ዓመታት በሰው ደረት ውስጥ ያለ እንከን የሚመታውን ሰው ሠራሽ ልብ ያየ ሰው አንድ ጥያቄ ብቻ ለመጠየቅ ይገደዳል፦ የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ምጥቀት መጨረሻው ወዴት ነው?
በእርግጥ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ተራ የቴክኖሎጂ ወሬ ሊመስል አሊያም ልቦለዳዊ የቢሆን ዓለም ነው ሊያስብል ይችላል ነገር ግን ይህ የሰው ልጅ ሕይወት እና የባህል ታሪክ በኤአይ (AI) አብዮት እየተጻፈ ያለበት ታሪካዊ ክስተት ነውና ጥያቄው የምር ጥያቄ ይሆናል እናም ትንሽ እንጠይቅ።
የኢትዮጵያ የቡና አፈላል ሥርዓት ተራ የዕለት ተዕለት ልማድ አይደለም፤ ቃላት ከሚገልጹት በላይ የጠለቀ የራሱ የሆነ ለዛ ያለው የማኅበራዊ ትስስራችን ጽኑ ማገር ነው።
በቀይ ፍም ላይ ሲታመስ አካባቢውን የሚያውደው የጥሬ ቡና መዓዛ፣ እንደ ልብ ትርታ የሚመታው የሙቀጫው ድምፅ፣ የዕጣኑ ጢስ፣ እንዲሁም ከጠቆረችው የሸክላ ጀበና ቀስ ብሎ ወደ ስኒዎቹ የሚንቆረቆረው ጥቁር ወርቅ ይህ ሁሉ ተዳምሮ የሰውን ልጅ መስተጋብር፣ አብሮነትንና ማህበረሰባዊ ትስስርን ለዘመናት ጠብቆ ያቆየ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው።
ታዲያ ይህንን መንፈስ እና በሰዎኛ ስሜት የተገመደ ጥልቅ ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ከአዲስ አበባ በሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው የቻይናዋ ኒንጃንግ ግዛት ኩንሻን ከተማ ውስጥ አንድ የብረት ሮቦት ሲያከናውነው መመልከት እጅግ አስገራሚና አስደምሞ የሚያስቀር ትዕይንት ነበር።
በቅርቡ በ"ቤልት ኤንድ ሮድ" የጋዜጠኞች የልምድ ልውውጥ ጉብኝት አካል ሆኜ፣ በኒዮን መብራቶች በደመቀች እጅግ ዘመናዊ ህንፃ ውስጥ በዓለም የመጀመሪያው የሮቦት መደብር ተብሎ በሚጠራው "Robot 6S Store" ተገኝቼ ነበር።
በዚያም እጅግ ዘመናዊ የሆነ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የሮቦት እጅ፣ የኢትዮጵያን ምርጥ ቡና ያለአንዳች የሰው ልጅ እርዳታ ያለምንም እንከን ሲፈጭ፣ ሲያዘጋጅ እና ሲያፈላ ተመለከትኩ።
ይህ አፍሪካዊ የግብርና ምርት እና የቻይና የላቀ የሮቦቲክስ ምህንድስና ውህደት ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ከሚታዩት የተለመዱ የዲጂታል ሞዴሎች በተለየ መልኩ ቻይና በሮቦቲክስ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ በዓለም ላይ እንዴት ግስጋሴ እያደረገች እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ታላቅ ክስተት ነው።
የቻይናውያን የቴክኖሎጂ ብቃት እና ሊወሰድ የሚገባው ትልቁ ተሞክሮ በችርቻሮ ንግድ እና በሮቦቲክስ ብቻ የተወሰነ አይደለም።
የቻይና የቴክኖሎጂ ዕድገት (ዝላይ) እውነተኛ ተዓምር የሰው ልጅን ሕይወት በመታደግ ረገድ የሚያደርገው ታላቅ አስተዋጽዖ ነው።
ከስምንት ዓመታት በፊት የቻይና ሳይንቲስቶች እና የቀዶ ጥገና ሐኪሞች እጅግ የረቀቀ የህክምና ምህንድስናን በመጠቀም በሀገር ውስጥ ያበለጸጉትን እና ሙሉ በሙሉ የሚሰራ ሰው ሠራሽ ልብ (Artificial Heart) በመጨረሻው ደረጃ የልብ ድካም ለሚሰቃዩ የ60 ዓመት አዛውንት በተሳካ ሁኔታ ገጥመውላቸዋል።
የሰውን የልብ ትርታ ያለምንም እንከን በሚከታተሉ እና በሚመስሉ ውስብስብ የኤአይ አልጎሪዝሞች የሚሰራው ሰው ሠራሽ ልብ የሰውየውን ሕይወት ከመታደግ አልፎ ዛሬ ከስምንት ዓመታት በኋላም በተረጋጋ ጤንነት እንዲኖሩ አስችሏቸዋል።
ቻይና ኤአይን በሕክምናው ዘርፍ በስፋት እና በከፍተኛ ስኬት እየተጠቀመችበት ሲሆን ይህ የላቀ ምህንድስናም በየሆስፒታሎቿ የባለሙያ እጥረትን ለመቅረፍ እና ህይወትን ለማዳን የራሷን የዲጂታል ሉዓላዊነት ያረጋገጠችበት ጎዳና ነው።
ይህ የቻይና አጠቃላይ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ለኢትዮጵያ ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል። ኢትዮጵያ ይህንን ዘመናዊ መፍትሄ ከውጭ እስኪመጣላት እጇን አጣጥፋ እየጠበቀች አይደለችም።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያው የመንግስት ተቋም ሆኖ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት (EAII)፣ የቻይናን ስኬታማ ፈለግ በመከተል የራሳችንን የሕክምና መፍትሄዎች በሀገር በቀል እውቀት እየገነባ ይገኛል።
ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) ጋር በመተባበር የሀገር ውስጥ መሃንዲሶች ከማሞግራፊ ምስሎች የጡት ካንሰርን እና የስኳር በሽታ ዓይነቶችን ለመለየት የተነደፉ የኤአይ ሞዴሎችን ሰርተው አጠናቀዋል። ገዳይ የሆኑ የልብ በሽታዎችን በቀጥታ ከኢሲጂ (ECG) ምልክቶች የሚለዩ ሞዴሎችንም በሙከራ ላይ ይገኛሉ።
ቻይና በኤአይ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የልህቀት ደረጃ ልትደርስ የቻለችው በገነባችው የሃርድዌር ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂውን በምታስተዳድርበት እጅግ ጠንካራ የሥነ-ምግባር ፍልስፍናም ጭምር ነው።
የፉዳን ዩኒቨርሲቲው ታዋቂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዤንግ ቻንግዦንግ የቻይናን መሠረታዊ የቴክኖሎጂ ሥነ-ምግባር አስተዳደር “የመጀመሪያውን ቁልፍ መቆለፍ” በሚል ጥልቅ ዘይቤ ይገልጹታል።
"የአንድን ሸሚዝ የመጀመሪያ ቁልፍ ስትቆልፍ ካሳሳትክ፣ ተከታዮቹ ቁልፎች በሙሉ የተንጋደዱ ይሆናሉ" ይላሉ ፕሮፌሰር ዤንግ።
ኢትዮጵያም "ዲጂታል ኢትዮጵያ" የተሰኘውን ስትራቴጂዋን ስታራምድ ልክ እንደቻይና በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ሃገራት ተሞክሮ በመውሰድ የራሷን "የመጀመሪያ ቁልፍ" በትክክል መቆለፍ እና የቴክኖሎጂ ሥነ-ምግባር ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ጀምራለች።
እውነተኛ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት እና ዲጂታል ሉዓላዊነት ያለ አካላዊ መሠረተ ልማት ሊታሰብ አይችልም። የራስህ የዳታ ማዕከል፣ ፈጣን የኢንተርኔት ግንኙነት እና ግዙፍ የማስላት አቅም ከሌለህ፣ የቴክኖሎጂው ሙሉ ባለቤት መሆን አትችልም።
ይህንን ትልቅ ፈተና በመገንዘብ ኢትዮጵያ የቻይናን የመሠረተ ልማት ግንባታ ልምድ በመቅሰም የራሷን የኮምፒውቲንግ የጀርባ አጥንት በከፍተኛ ሁኔታ እየገነባች ነው።
የኤአይ ኢንስቲትዩቱ 99.98% አስተማማኝነት ያለው 15 ፔታባይት የዳታ ማከማቻ፣ 13,000 የኮምፒውቲሽናል ቨርቹዋል ማሽኖች፣ እና 8,000 ጂፒዩዎች ያሉት ግዙፍ የዳታ ማዕከል (Tier-3 Data center) ዘርግቷል።
በአዲስ አበባ ከተገነባው የዊንጉ አፍሪካ የንግድ ዳታ ማዕከል ጋር በመተባበርም የራሳችንን መረጃዎች በራሳችን አስተማማኝ ማዕከላት እያስተናገድን እንገኛለን።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ሮቦቲክስ በከፍተኛ ፍጥነት እየመጠቁ በሚሄዱበት ወቅት የሥራ እድል መቀነስን በተመለከተ የሚነሱ ስጋቶች አሉ።
ለዚህ ጥያቄ ፕሮፌሰር ዤንግ፣ "መታነቅን በመፍራት ከመብላት ወደኋላ ማለት የለብንም" የሚል አበረታች ምክር ይሰጣሉ።
ቻይና እንዳደረገችው ሁሉ እኛም ወጣቶቻችንን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ብቻ ከመሆን ወደ ንቁ የኤአይ ፈጣሪዎች ማሸጋገር አለብን።
በኤአይ ኢንስቲትዩቱ የስታርትአፕ ማዕከል እና በቅርቡ በዩኤንዲፒ ድጋፍ በተከፈተው "AI UniPod" አማካኝነት፣ ከ200 በላይ የሀገር ውስጥ ወጣት ፈጣሪዎች የራሳቸውን መፍትሄዎች እያሳደጉ ይገኛሉ።
በቻይና ኩንሻን ከተማ የሮቦት እጅ የኢትዮጵያን ቡና ሲያፈላ ማየት የዘመናዊ የቻይና ምህንድስና እፁብ ድንቅ ስራ መሆኑ አያጠያይቅም።
በተመሳሳይ በአንድ የ60 ዓመት አዛውንት ደረት ውስጥ የሚመታው የቻይናውያን ሰው ሠራሽ ልብ የሳይንስ ተዓምር እና ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ ደህንነት ሲውል የሚያመጣው እምቅ አቅም መገለጫ ነው።
ያ ሮቦት ያፈላውን ቡና ስጠጣ አንድ ነገር በግልፅ ታይቶኛል፤ ቴክኖሎጂ አንድን ሂደት ያለምንም እንከን ሊፈጽም ይችላል፤ ነገር ግን የዚያን ቴክኖሎጂ ዓላማ እና ትርጉም መወሰን ያለበት የሰው ልጅ ነው።
ቻይና ያካበተችው ስኬታማ የኤአይ እና የሮቦቲክስ ልምድ ያበረከተችው የቴክኖሎጂ አስተዳደር ጥበብ እና ለሰው ልጅ ደህንነት የምትሰጠው ትኩረት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ ትልቅ ብርሃን ፈንጥቋል።
የራሳችን የዳታ ማዕከላት እየሰሩ፣ ተቋሞቻችን የህዝብን ጤና እያሻሻሉ እና ህይወት እያዳኑ፣ እንዲሁም ወጣቶቻችን በሀገር በቀል ቋንቋዎች አልጎሪዝሞችን እየጻፉ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከቻይና ልህቀት ትምህርት በመውሰድ የራሷን የዲጂታል ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ በመገንባት ላይ ትገኛለች።
የኢትዮ-ቻይና አጋርነታችንን ይበልጥ በማጠናከር የጋራ እና ብሩህ የዲጂታል ዘመን ዕጣ ፈንታችንን እውን እናደርጋለን።
በነቢዩ ወንድወሰን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: