የቻይና ተመራማሪዎች የህዋ ቴክኖሎጂን ወደ አዲስ ደረጃ የሚያሸጋግር ትልቅ ስኬት አስመዝግበዋል። ቀደም ሲል ሳተላይቶች የሚሰሩት አንድ የተወሰነ አገልግሎት ብቻ ቢሆንም (ለምሳሌ ምስል ማንሳት ብቻ ወይም የቴሌኮም መረጃ ማስተላለፍ)፣ አሁን ግን መገናኛን፣ ዳሰሳን፣ ማስላትን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሂደትን በአንድ ላይ የሚያጣጥም ባለብዙ ተግባር ሥርዓት እውን አድርገዋል።
ለዚህ አዲስ ስኬት ማሳያ የሆነችው ፔጋሱስ 1 (PEGA-SUS1) የተሰኘችው 150 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሳተላይት ናት።
ሳተላይቷ በሼንዘን የሚገኘው ፔንግቼንግ ላብራቶሪ፣ በቤጂንግ የሚገኘው ጋላክሲ ስፔስ የግል ኩባንያ እና ሌሎች የምርምር ተቋማት በጋራ የበለጸገች ሲሆን በቻይና የንግድ ሮኬት አማካኝነት ከሌሎች 8 ሳተላይቶች ጋር ወደ ህዋ ተልካለች።
የዚች ሳተላይት ዋና ልዩነቷ መረጃን ከህዋ ወደ መሬት ካወረደ በኋላ መተንተን ሳይሆን መረጃውን እዚያው ህዋ ላይ እያለች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ራሷ ማቀናበር መቻሏ ነው።
እንደ ጋላክሲ ስፔስ ከፍተኛ ቴክኒክ ባለሙያ ሬን ጂያዶንግ ገለጻ ለምሳሌ የደን ቃጠሎ ቢከሰት ሳተላይቷ የቃጠሎውን መኖር እና የጉዳቱን መጠን እዚያው ህዋ ላይ አጠናቅራ ዋናውን ውጤት ብቻ በፍጥነት ወደ መሬት ትልካለች።
ይህም ጥሬ ምስሎችን ሙሉ በሙሉ መላክ ስላይስፈልግ የማስተላለፊያ ጊዜን እና የመረጃ መጠንን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።
አዲሷ ፔጋሱስ 1 (PEGA-SUS1) ሳተላይት በአጠቃላይ ዘጠኝ ሳተላይቶችን እንደሚያካትት በተገለጸው ስብስብ ውስጥ የመጀመሪያዋ ፈር ቀዳጅ ናት።
በቀጣይም ለ6G ቴክኖሎጂ እና ለቻይና የሳተላይት ኢንተርኔት ፈጠራ ትልቅ መሠረት በመጣል ከመሬት እስከ ህዋ የሚዘልቅ የተቀናጀ የመገናኛ መረብ ለመገንባት መንገድ ትከፍታለች ተብሎ ተስፋ ተይዟል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: