ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ ኣቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት፤
በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ ኣምላክ ኣሜን፡-
ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰብዓዊ ክዋኔው ሰው ቢሆንም በመለኮታዊ ክዋኔው የኣብና የመንፈስ ቅዱስ ቃል ወይም ወልደ እግዚአብሔር ነው፤
በመሆኑም በሰብዓዊ ክዋኔው መዋች ሲሆን፣ በመለኮታዊ ክዋኔው ተነሽና ኣንሺ ነው፤ ከዚህ አንጻር ሥግው ቃል ሁለቱንም ተግባራት በአንድ አካልና ክዋኔ የመፈጸም ሥልጣን አለው፤ ይህም በመሆኑ ራሴን የማኖርና የማንሣት ሥልጣን አለኝ በማለት እውነታውንና ምንነቱን አሳየ፤
ጌታችን ይህንን አስመልክቶ ከመሞቱና ከመነሣቱ በፊት ለቅዱሳን ሓዋርያት በተደጋጋሚ ኣስረድቶኣል፤ ስለሆነም የጌታችን ሞትና ትንሣኤ ድንገተኛና የግድ ሳይሆን ታውቆ ያደረና የውድ እንደሆነ ከዚህ እውነታ እንረዳለን፤
ጌታችን ይህንን ተግባር በውድ ፈቃዱ የፈጸመው በእግዚአብሔር አሰራር ከዚህ ውጭ የዓለም ድኅነት የሚከናወንበት ዕድል ስለሌለ ነው፤ በእግዚአብሔር አሰራር ኃጢአትና በደል የሚሰረዘው በቤዛዊ መሥዋዕት ብቻ እንደሆነ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በነበረው የቤዛዊ መሥዋዕት አቀራረብ የታወቀ ነው፤
በመሆኑም የሰውን ምልአተ ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ሰርዞ ሰውን ከሞት ቅጣት ነጻ ለማውጣት ብቃት ያለው ቤዛዊ መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነበረበት፤ ይሁን እንጂ ለዚህ ዓይነቱ ቤዛዊ መሥዋዕት ብቁ የሆነ ከፍጡራን ወገን ስላልተገኘ ‹‹ለሊሁ መሥዋዕት፣ ወለሊሁ ሠዋዒ፣ ወለሊሁ ተወካፌ መሥዋዕት
ማለትም›› ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ መሥዋዕት ኣቅራቢ ሊቀ ካህናት፣ ራሱ ተወካፌ መሥዋዕት ኣምላክ ሆኖ የቤዛነታችንን መሥዋዕት ራሱ በራሱ ለራሱ ኣቀረበ››፤
በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕትም እኛን ከሞት ቅጣት ነጻ ኣደረገን፤ ትንሣኤያችንንም በትንሣኤው አበሰረ፤ በክርስትና ሃይማኖት የሚገኝ ፍጹም ድኅነትና ነጻነት በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ ነው፤
የተወዳደችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምእመናንና ምእመናት!
ጌታችን በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ሲያበስረን የትንሣኤ ሰዎች ሆነን በመንፈስና በሞራል በማደግ ብርሃናተ ዓለም ልንሆን እንጂ እንደገና የጨለማው ኃይል መሳሪያዎች ልንሆን አይደለም፤ የሞቱና የትንሣኤው ምስጢር በንጹሁ ኅሊናችን ካስተዋልነው ውስጣችን እሱን ለመቀበል የሚያዳግተው አይደለም፤
ከዚህ ኣንጻር በትንሣኤው አምነን ትንሣኤያችንን እየተጠባበቅን የምንገኝ ሕዝበ ክርስቲያን በቅን አስተሳሰብ፣ በርቱዕ ኣእምሮና በኃይለ ሃይማኖት እየታገዝን ጨለማውን ዓለም ወደብርሃን ለመለወጥ መጣርና መትጋት ይጠበቅብናል፤
የጨለማው ዓለም መንፈስ ሊያጠፋን ካልሆነ በቀር እንደማይጠቅመን በተጨባጭ የምናውቀው ነው፤ ወደድንም ጠላንም ያለን ብቸኛ አማራጭ ብርሃንን መከተል ነው፤ እሱም እግዚአብሔር ነው፤በብርሃን የሚመላለስ እንደማይጐዳ በእግዚአብሔር የሚኖርም ተጐድቶ ኣያውቅምና ነው፤
ዓለም እንደ አጠቃላይ በጨለማ ተውጦ ሲተረማመስ የሚታየው ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ምርጫው ስላደረገ ነው፤ ስለሆነም የኛ ምርጫ ብርሃን የሆነውን እግዚአብሔር እንዲሆን የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ጥሪ ነው፤
በመጨረሻም፡-
የትንሣኤ በዓላችንን ስናከብር ዓለም በክፋቱ ያጨለመባቸውን ወገኖች ጦማችው እንዳይውሉ ካለን ከፍለን የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስና የዕለቱ ደስታ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ቀኑ ለሁላችንም ፍጹም ብርሃን ሆኖ ይውል ዘንድ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን በእግዚአብሑር ስም እናስተላልፋለን፤
መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን!!
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”
ኣሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ሚያዝያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ