አፍሪካ የራሷን ሀብት ለራሷ ልማት የምታውልበትን አዲስና ፍትሃዊ የታክስ ሥርዓት ዕውን ለማድረግ የሚያስችል መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ከመቶ ዓመታት በላይ በ38 የበለጸጉ ሀገራት ብቻ ሲዘወር የቆየውን ዓለም አቀፍ የታክስ ሥርዓት በመቀየር፣ ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውሳኔዎች ላይ ተመልካች ሳይሆኑ ወሳኝ የሚሆኑበት አዲስ የታክስ ትብብር ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ይገኛል።
ማዕቀፉ ሁሉንም 193 የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ በፈረንጆቹ 2023 በአፍሪካ ሀገራት ቡድን አነሳሽነት ተጀምሮ እስካሁን አምስት ዙር ድርድሮች የተደረጉበትን ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ አስመልክቶ፣ ከአሥር ቀናት በኋላ በናይሮቢ ለሚካሄደው ስድስተኛው ዙር ድርድር የአፍሪካ ሀገራትን አቋም ለማጠናከር ያለመ የከፍተኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች መድረክ ነው ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት (UN RCO)፣ በተመድ የልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የአፍሪካ ቀጣና (UN DCO) እና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) በጋራ የተዘጋጀው ይህ መድረክ፣ በፈረንጆቹ መስከረም 2027 ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀውን ታሪካዊ ስምምነት ለማሳካት የአህጉሪቱን የጋራ አቋም ለማቀናጀት ያለመ ነው።
አዲሱ የታክስ ትብብር ማዕቀፍ የታክስ ህግ በጥቂት ሀብታም ሀገራት ሳይሆን፣ በሁሉም ሀገራት እኩል ውሳኔ እንዲወጣ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ቢሮ ባይኖራቸውም እንኳ ገቢ ባገኙበት ሀገር ታክስ እንዲከፍሉ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ትርፋቸውን ወደ ውጭ ከማሸሻቸው በፊት ገቢ ባገኙበት ታዳጊ ሀገር ተገቢውን ታክስ እንዲከፍሉ ያስገድዳል።
በተጨማሪም አፍሪካ በየዓመቱ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት የምታጣውን ወደ 89 ቢሊዮን ዶላር ለማስቀረትና በታዳጊ ሀገራትና በትላልቅ ኩባንያዎች መካከል የሚነሱ የታክስ አለመግባባቶች በፍትሃዊነት እንዲፈቱ በማስቻል፣ አህጉሪቱ የራሷን ሀብት ለራሷ ልማት የምታውልበትን አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
በጌታቸር ጥበቡ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: