አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ የልብ ትርታ በመሆን የታሪክና የዘመናዊነት መገናኛነቷን እያረጋገጠች ትገኛለች።
በአሁኑ ወቅት ከተማዋ በከፍተኛ የልማት አብዮት ውስጥ እያለፈች ሲሆን፣ በአህጉሪቱ ተወዳዳሪ የሌላት የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን ዳግም ተውባ ቀርባለች።
ይህን አዲስ ገጽታዋን የታዘቡት እንደ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ያሉ ታዋቂ መሪዎች፣ እንዲሁም ከጋና እና ከኬንያ የመጡ የሕግ አውጪዎች በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በአድናቆት መመልከታቸው የለውጡ ማሳያ ነው። ከተማዋ የጀመረችው የልማት ንቅናቄ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኚዎች ደግሞ ተመራጭ መዳረሻ እያደረጋት ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደሚሉት፣ ከተማዋ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ብትሆንም ቀደም ሲል በጽዳትና በውበት ጉድለት ምክንያት ይህ ደረጃዋ ጥያቄ ውስጥ ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጁ የጽዳት፣ የውበት እና የመሰረተ ልማት ሥራዎች አዲስ አበባ ዛሬ በአፍሪካ ካሉ 10 ጽዱ ከተሞች ተርታ መሰለፍ ችላለች።
ይህ ለውጥ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እድገት እንደ መሰረታዊ ምሰሶ ሆኖ እያገለገለ ሲሆን፣ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ መዲናዋ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን አስተናግዳለች። የዘንድሮው አፈጻጸም ደግሞ በግማሽ ዓመቱ የባለፈውን ዓመት ሙሉ ሪከርድ የደረሰ በመሆኑ፣ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ቁጥሩ በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደረጋት ትልቁ ሚስጥር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሲሆን፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምና አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ከተከፈቱ ጀምሮ በየቀኑ በዝግጅቶች ተይዘው መዋላቸው የፍላጎቱን መጨመር ያሳያል።
በመስቀል አደባባይ፣ በዓድዋና በዩኒቲ ፓርክ የተገነቡ ዘመናዊ መኪና ማቆሚያዎች ለጉባኤ ተሳታፊዎች ልዩ ምቾትን ከመፍጠራቸውም ባለፈ፣ ከተማዋን ወደ "ስማርት ሲቲ" ለመቀየር የተጀመሩ የዲጂታል አገልግሎቶችና የትራንስፖርት ዘመናዊነት ለዘርፉ ትልቅ እሴት ጨምረዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማደግ በሆቴሎች፣ በትራንስፖርትና በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ የገቢ መነቃቃት መፍጠሩን ከንቲባዋ ሲያስረዱ፣ እንግዶች ወደ ከተማዋ ሲመጡ የሚገበያዩትና የሚጠቀሙት አገልግሎት ለዜጎች ሰፊ የኢኮኖሚ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ዛሬ አዲስ አበባ የራሷን ችግር መፍታት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አፍሪካውያን አርአያ እየሆነች ሲሆን፣ እስካሁን 19 የሚጠጉ ሀገራት የመዲናዋን የኮሪደር ልማትና የፕሮጀክት አፈጻጸም ፍጥነትን ለመቀሰም መምጣታቸው ለዚህ ተጠቃሽ ማስረጃ ነው።
ከተማዋ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ብቻ ሳትወሰን የጤና ቱሪዝም ማእከል የማድረግ ታላቅ ራእይም ሰንቃለች፤ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሦስት ትልልቅ ሆስፒታሎች በዘመናዊ ግብዓትና በባለሙያ ተሟልተው ሲከፈቱ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ቁልፍ የሕክምና መዳረሻ ትሆናለች።
የከተማዋ ስኬት በዓለም አቀፍ መድረኮች እውቅና ማግኘቱን ቀጥሏል። በሉዛን ስዊዘርላንድ በተካሄደው 88ኛው ዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS) ጉባኤ ላይ፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን 89ኛውን ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመርጣለች።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተደማጭነት ያላቸው የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ መሰብሰባቸው ከተማዋንና ሃገራችንን ለዓለም ይበልጥ ለማስተዋወቅ ታላቅ እድል ይፈጥራል።
አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ጉዞው በጽኑ መሰረት ላይ የቆመ በመሆኑ፣ ይህች የዲፕሎማሲያዊቷ የውበት ተምሳሌት የአፍሪካ ኩራት ሆና መዝለቋን ትቀጥላለች።
በላሉ ኢታላ