Search

በአንድ ደቂቃ ውስጥ የአልዛይመር ቅድመ-ምልክቶችን የሚለየው ሰው ሠራሽ አስተውሎት

ሓሙስ ሚያዝያ 08, 2018 79

በአሜሪካ ተመራማሪዎች ባካሄዱት ጥናት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም  የአልዛይመር ሕመም ቅድመ-ምልክቶችን በአንድ ደቂቃ ውስጥ መለየት እንደሚቻል ተገልጿል።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ፥ ቴክኖሎጂው ሰዎች በቃላት ምርጫቸው፣ በንግግር ፍሰታቸው እና በዓረፍተ ነገር አወቃቀራቸው ላይ የሚያሳዩዋቸውን ለውጦች መሠረት በማድረግ የመለየት አቅም አለው።

በተለምዷዊው መንገድ የሚካሄዱ የአልዛይመር ቅድመ-ምልክት ምርመራዎችን ይተካል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይህ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እጅግ ቀላል፣ ፈጣን እና ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑም ተነግሮለታል።

እስካሁን በሕክምናው ዘርፍ ለአገልግሎት እየዋሉ ያሉ የአልዛይመር መመርመሪያ ዘዴዎች ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ከመሆናቸውም በላይ፣ አልፎ አልፎ በባለሙያዎች የግል ምልከታ ላይ የሚመሠረቱ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል።

አልዛይመር ቀስ በቀስ የሰውን ልጅ የማስታወስና የማሰብ ችሎታ በመቀነስ የዕለት ተዕለት የሕይወት ዘይቤን የሚያዛባና በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ የሚስተዋል ሕመም ነው።

አዲሱ ቴክኖሎጂ በሽታው አስቀድሞ እንዲታወቅ እና አስፈላጊው ሕክምና በወቅቱ እንዲጀመር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የሳይቴክ መረጃ ያመላክታል።

በዓለም ዙሪያ በዚህ ሕመም የሚጠቁ ሰዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሆነ የሚገመት ሲሆን፣ በአሜሪካ ብቻ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ከ7 ሚሊዮን በላይ ሕሙማን እንዳሉ ጥናቱ ጠቁሟል።

በልዩ እሸቱ

#EBC #AlzheimersDetection #AI #HealthInnovation #MedicalTechnology