Search

የፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር አዋጅ በሙሉ ድምፅ ጸደቀ

ማክሰኞ ሚያዝያ 13, 2018 324

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የስፖርት ዘርፍ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበትን የፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል።
አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1413/2018 በስፖርቱ ዘርፍ አካታች፣ ዘመናዊና ግልጽነት ያለው የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት ምቹ መደላድል የሚፈጥር ሲሆን፣ በዘርፉ የሚታዩ የአሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ታላቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
አዋጁ የስፖርት መሠረተ ልማቶችንና ማሰልጠኛ ተቋማትን ከማስፋፋት ባለፈ፣ የስፖርት ግብዓት አምራቾች እንዲበረታቱና ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት ያደርጋል።
በተጨማሪም ማህበራዊ ትስስርን በማጎልበት፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማጠናከር እና ስፖርት ነክ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት በምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ አብራርተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በምክር ቤቱ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ስፖርት የኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ እንዲሆን ዘርፉን የያዙ ማነቆዎችን በአሰራርና በስርዓት መፍታት የግድ እንደሚል ጠቁመዋል።
አዋጁ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ በማድረግ ረገድ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የአዋጁን አስፈላጊነት በማመንና አፈጻጸሙ ላይ ትኩረት እንዲደረግ በማሳሰብ አዋጁን በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።