በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ በተመረቀው የእንጦጦ እስከ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ ለአካባቢው ታታሪ ማህበረሰብ መስራት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የቀጨኔና እንጦጦ ነዋሪዎች በሸማና ሸክላ ስራ የሚደነቁ ቢሆንም የሚገባቸውን ክብር አላገኙም ያሉት ከንቲባዋ፣ ፕሮጀክቱ ይህንን የተሳሳተ አመለካከት እንደሚቀይር ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል የሚመረተውን አክምባሎ በማስታወስ፣ የእጅ ጥበብ ስራዎች ለጎብኚዎች የሚቀርቡባቸው ሱቆች መዘጋጀታቸውንና የባህል ማስታወሻ ቅርጻ ቅርጾች መካተታቸው ለአካባቢው ሙያተኞች “ስራችሁ ክቡር እንጂ የሚታፈርበት አይደለም” የሚል መልዕክት ያስተላለፈ መሆኑን ገልጸዋል።
አካባቢው በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ በዚህ ልማት አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ እስከ 10 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል አግኝተዋል።

ወጣቶችም ከአደገኛ ሁኔታዎች ርቀው በካፌዎች፣ ልብስ ስራና ስፖርት ማዕከላት ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
እያንዳንዱ ተቋም የራሱ ታሪክ እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፣ የሀገር ባህልን ከሚያንጸባርቁ ቅርጻ ቅርጾች ባሻገር የኢትዮጵያን ክብር ያሳዩ አትሌቶችን የሚዘክሩ ሃውልቶችም ተቀምጠዋል። ከንቲባዋ ነዋሪዎች የጋራ ሀብታቸው የሆነውን ስፍራ እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ለማህበረሰቡ፣ ለወጣት ኮንትራክተሮችና ፕሮጀክቱን በግንባር ቀደምትነት ላስተባበሩት የከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ምስጋና አቅርበው፣ ወንዙን በማጽዳት ሂደት የተከፈለውን መስዋዕትነት አድንቀዋል።
የተሰራው ስራ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን በመግለጽም “እኛ እናልፋለን፤ ታሪክ ግን አያልፍም” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በልዩ እሸቱ