ቴክቦል የእግር ኳስ ክህሎትን ከጠረጴዛ ቴኒስ ሕግጋት ጋር አጣምሮ የያዘ፣ ኳሱ በእጅ ሳይነካ በታጠፈ ጠረጴዛ ላይ የሚጫወቱት አስደሳች ስፖርት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ተወዳጅነትን እያገኘ የመጣ የስፖርት አይነት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በይፋ ያስመረቁት ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለው የመልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ይህንን የስፖርት ዓይነት ያካተተ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ2012 በሃንጋሪ የተዋወቀ የስፖርት አይነት ሲሆን፣ ጋቦር ቦርሳኒ፣ ቪክቶር ሁሳር እና ጂዮርጂ ጋትያን በተባሉ ሦስት ግለሰቦች አማካኝነት እንደተጀመረ ይገለፃል።

የቴክቦል ዋነኛው መለያ ባህሪ "ቴክቦርድ" (Teqboard) ተብሎ የሚጠራውና መሃሉ ከፍ ብሎ ጫፎቹ ወደ ታች የታጠፈ ልዩ ጠረጴዛ መሆኑ ነው። ይህ የጠረጴዛው ቅርጽ ኳሱ በየትኛውም አቅጣጫ እንዲነጥርና ጨዋታው ፍጥነትና ከፍተኛ ክህሎት እንዲኖረው ያደርጋል።
የስፖርቱ ሕጎች በጣም ቀላልና ለማንም ሰው ለመረዳት ምቹ ሲሆኑ፣ በሁለት ተቃራኒ ተጫዋቾች (አንድ ለአንድ) ወይም በቡድን (ሁለት ለሁለት) ሊጫወቱት የሚችሉት ስፖርት ነው።
ልክ እንደ እግር ኳስ ሁሉ፣ ኳሱን በእጅ መንካት በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፤ ተጫዋቾች ኳሱን በጭንቅላታቸው፣ በደረታቸው፣ በትከሻቸው ወይም በእግራቸው መምታት ይችላሉ።
አንድ ተጫዋች ወይም ቡድን ኳሱ ወደ ተቃራኒው ወገን ከመሻገሩ በፊት ቢበዛ ሦስት ጊዜ ብቻ የመንካት መብት አለው።
በአንድ የሰውነት ክፍል (በእግር ብቻ፣ በደረት ብቻ አልያም በጭንቅላት ብቻ) በተከታታይ ሁለትጊዜ ኳሱን መንካት አይፈቀድም። ይህም ተጫዋቾች የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን እንዲጠቀሙና የተለየ ብቃት እንዲያሳዩ ያስገድዳቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ቴክቦል በዓለም አቀፍ ደረጃ በፌዴሬሽን የሚመራ ሲሆን፣ ወደ ኦሎምፒክ ስፖርቶች እንዲካተትም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። እንደ ሮናልዲንሆ ያሉ ታዋቂ የዓለም እግር ኳስ ተጫዋቾች የስፖርቱ አምባሳደር በመሆን እያስተዋወቁት ይገኛሉ።
ስፖርቱ ምንም ዓይነት የአካል ንክኪ ስለሌለውና በትንሽ ቦታ ላይ ሊከናወን ስለሚችል ጉዳትን የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ ለተጫዋቾች ትኩረትን፣ ቅልጥፍናን እና የኳስ ቁጥጥርን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በተጨማሪም የልብ ጤናን የሚያሻሽል፣ አእምሮን የሚያነቃቃ እንዲሁም የአይን፣ የእግር እና የአእምሮ ቅንጅትን በማሳደግ ፈጣን ውሳኔ የመስጠት ብቃትን የሚያዳብር ስፖርት ነው፤ ዕድሜና ጾታ ሳይለይ ሁሉም ሰው ሊጫወተው ስለሚችል፣ የአእምሮ ውጥረትን ለመቀነስና ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በዘረንቶስ ሰለሞን