Search

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ናቸው - የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 119

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የቡድኑን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጀመሪያ ግምገማ ውጤትን በተመለከተ መግለጫ በሰጡበት ውቅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዴሞክራሲን ለማጎልበት የሠራውን ሥራ እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።

አጠቃላይ የምርጫው ሂደትም የኢትዮጵያን እና የዓለም አቀፍ ሕጎች ማዕቀፍን በተከተለ መልኩ መካሄዱን በግምገማው ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።

ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ የነበረው ሂደት አበረታች እንደነበር የገለጹት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ከምርጫው ዋዜማ አንሥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የመራጮች ትምህርት አሰጣጥ በተመለከተም ሕዝቡ እንዴት መምረጥ እንዳለበት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኝ መደረጉን እና በምርጫው ዕለት የነበረው የተቀናጀ መናበብ ለመራጮች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን አስረድተዋል።

በምርጫው ሂደት ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂ በተለይም ለወጣቶች የፈጠረው ዕድል ከፍተኛ መሆኑን የታዛቢ ቡድኑ መሪ በመግለጫቸው አብራርተዋል።

የድምፅ መስጫ ሰዓት መራዘሙ ለመራጮች ተጨማሪ ዕድል መፍጠሩን፣ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን በድምፅ አሰጣጡ ሂደት ቅድሚያ መሰጠቱ የዜጎችን ተሳትፎ በእጅጉ ማነቃቃቱንም ጠቁመዋል።

በመላው ኢትዮጵያ የምርጫ አስፈፃሚዎች እና የፀጥታ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በጥሩ ሁኔታ መወጣታቸውን፣ የመገናኛ ብዙኃንም በተመሳሳይ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት ሥራቸውን ማከናወናቸውን አድንቀዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው ያሳየው ተሳትፎ እና ትልቁን ኃላፊነቱን በጀግንነት መወጣቱ እጅግ የሚያስመሰግን መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ አስታውቀዋል።

በለሚ ታደሰ