Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአርሲ ዞን በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ገልጸዋል - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 64

በኦነግ ሸኔ ዐማጽያን በንጹሐን ዜጎች ላይ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ዒላማ ተደርገው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ፤ የቤተሰብ እና የወዳጆቻቸውን ሕይወት ላጡ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው በአርሲ ዞን ለሚገኙ ወገኖቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻሉ ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት አስታወቀ።

/ቤቱ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ እነዚህ ጥቃቶች የሀገራችንን ብሔራዊ ዕድገት ለማደናቀፍ ከሚሹ አካላት፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ አማፂ ቡድኖች እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ጥላቻ ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጥምረት የተከናወኑ ሲሆኑ፤ ዓላማቸውም በኢትዮጵያ አለመረጋጋትን እና የምርጫ መስተጓጎልን ለመፍጠር ሲደረግ የነበረው የጥፋት ውጥን ተከታይ ነው ብሏል።

መንግሥት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር ፍትሐዊ እና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ልዩ ትኩረት እና ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት ሲሠራ መቆየቱን መግለጫው አስታውሷል።

በሌላ በኩል የጥፋት ኃይሎች ከባዕዳን ጋርፅምዶ' የሚል ቁርኝት በመፍጠር ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሰፊ የጥፋት ዝግጅት ሲያድርጉ ቆይተዋል፣ ሀገራዊ ምርጫው እንዳይከናወን ሰፊ ርብርብ አድርገዋል።

በተጨባጭም በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የዜጎችን የመምረጥ መብት እና ነጻነት ለመጋፋትና ለማደናቀፍ አለን የሚሉትን የጥፋት እጅ ዘርግተዋል። 

እነዚህ የጠላት ኃይሎች በመደጋገፍና በመናበብ ዐመፅና ሁከት ለማነሳሳት፣ ከተሞችን በሽብር ጥቃት ለማወክ፣ በመንገዶች የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥለው ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል።

እንደ ማሳያ የጦር መሣሪያ፣ ተተኳሾችን እና ሌሎች ሎጀስቲክሶችን በድጋፍ በማቅረብ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመዋል፤ በአማራ ክልል ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ወልድያ ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እና ሲቪሎች ላይ ዒላማ በማድረግ የሽብር ዝግጅት አድርገዋል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ባደራጇቸው የኅቡዕ ሴሎች አማካኝነት በተመረጡ አከባቢዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፤ ቢሆንም ይህ የጥፋት ሴራ እና ድርጊት እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሸኔ ሽብር ቡድን ከጽንፈኛው ፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር በመናበብ በአንዳንድ አካባቢዎች መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴ ለማስቆምና ለማስተጓጎል የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት የተጠናከረ እርምጃ ፍላጎቱን ማሳካት አልቻለም።

ቡድኑ በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደበትን ርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ እና ፍላጎቱን ማሳካት ባለመቻሉ ስስ ዒላማዎች ላይ ያተኮረ ርምጃ በመውሰድ የሃይማኖት እና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ በማለም በአርሲ ዞን አሰኮ እና አካባቢው ጥቃት በመፈጸም ሁሉን ዓይነት የጥፋት ርብርብ ያደረገ ቢሆንም፤ ሁኔታውን በመቆጣጠር የፀጥታ ኃይላችን በእነዚህ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

መንግሥት መሰል ሥጋቶችን በንቃት በመከታተል ላይ ሲሆን፣ በምርጫው ወቅትም በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች የተቀነባበሩ ተመሳሳይ ዕቅዶችን በስኬት ማክሸፍ ችሏል።

በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፤ ፍርሃትና ክፍፍልን ከሚያጎሉ የሚዲያ ዘመቻዎች ጋር በማስተሣሠር የተቀነባበረው ይህ እኩይ ተግባር፤ በመንግሥት የደኅንነት መዋቅርና ኦፕሬሽኖች አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስተጓጎል ተደርጓል።

ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ ክፍፍልን ለመዝራት የኃይል ጥቃትን እና ውድመትን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙ አካላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በግልጽ ሊወገዙ ይገባል።

መሰል ተግባራት በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የወደፊት ዕድል እንደሌላቸው ለማሳየት የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ በመስጠት ወሳኝ ርምጃችን ይቀጥላል።

በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት፣ ድርጊታቸውን ምክንያታዊ ለማስመሰል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ንግግር ቢጠቀሙ፤ ወሳኝ ዓላማን እያሳኩ ሳይሆን ወንጀል እየፈጸሙ ነው።

የፖለቲካ ቅሬታዎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ በብሔራዊ ምክክር ሂደት እና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት አማካኝነት መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ እና ሊያገኙ የሚገባቸው ናቸው ብሏል የጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት በመግለጫው።