የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በምክር ቤቱ ስር የሚንቀሳቀሱም ሆኑ በምርጫው የተሳተፉ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሂደቱ ላሳዩት ከፍተኛ የፖለቲካ ጨዋነት፣ ለሰላማዊ የሃሳብ ፉክክርና ለሕግ የበላይነት መገዛት የሚደነቅ መሆኑን ገልጿል።
ምክር ቤቱ በመግለጫው፣ ይህ የሰለጠነ አካሄድ ለዜጎች ሰፊ የአማራጭ አድማስ ከመፍጠሩም በላይ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አስገንዝቧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ ወጥተው የሰጡትን ድምፅና ያሳዩትን ምርጫ በሙሉ ልብ በመቀበል፣ ለሕዝብ ድምፅ ያለውን ፍጹም ክብርና እውቅና አረጋግጧል።
የምርጫ አሸናፊው የብልፅግና ፓርቲ የከተማዋንና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ በሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ላይ፣ የጋራ ምክር ቤቱ በነቃ ተሳትፎ፣ በገንቢ ሂስና በአማራጭ ሃሳቦች አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅን ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፏል።
የጋራ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተጠናቆ የብልፅግና ፓርቲ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ማሸነፉን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ይህ ምርጫ የከተማዋንና የሀገሪቱን የፖለቲካ ብስለት እንዲሁም የሕዝብን የሉዓላዊነት ስልጣን ያረጋገጠ ታሪካዊ መድረክ መሆኑን በጽኑ እንደሚያምን ገልጾ፣ በሕዝብ ነፃ ውሳኔ አሸናፊ ለሆነው ለብልፅግና ፓርቲ እና በውድድሩ ተሳትፈው የምክር ቤት ወንበር ላገኙ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ ስም ልባዊ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ታሪካዊው ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅና የዲሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት በውድድሩ የተሳተፉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ላበረከቱት አወንታዊና ታሪካዊ አስተዋጽኦ ምክር ቤቱ የላቀ ምስጋና አቅርቧል።
የምርጫው ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ ቢጠናቀቅም፣ የሀገር ግንባታ እና የሕዝብ አገልግሎት ቀጣይነት ያለው የጋራ ሃላፊነት በመሆኑ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አሳስቧል።
አሸናፊው የብልፅግና ፓርቲ የከተማዋንና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ በሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ላይ፣ የጋራ ምክር ቤቱ በነቃ ተሳትፎ፣ በገንቢ ሂስና በአማራጭ ሃሳቦች አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ምክር ቤቱ በውድድሩ ተሳትፈው የምክር ቤት ወንበር ላገኙ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም በድጋሚ ለብልፅግና ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ብሏል።
መላው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ለሰላማዊው የምርጫ ሂደት ስኬት ላደረጉት ታሪካዊ አስተዋጽኦም ምስጋናውን አቅርቧል።