Search

የሙሐመድ ሳላህ ቀጣይ ማረፊያ የት ይሆን?

ዓርብ ሰኔ 19, 2018 66

በመጨረሻም ስንብት ሆኗል። አንፊልድ ይህን ልጇን አትዘነጋውም። ለበርካታ ዓመታት ከተናጠቡበት ስኬት ጋር የተገናኙት አንድም በእርሱ ነውና፤ ሊቨርፑላውያን አብረው ያሳለፉትን በጎ ትዝታቸውን ሰንቀው፣ ነገስ ምን ይሆናል? የሚለውን ጥያቄያቸውንም ይዘው በእንባ ነበር “ደህና ሁን” ያሉት።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት የዓለም እግር ኳስ ትልቁ መነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መሀል የሙሐመድ ሳላህ ቀጣይ እጣ ፈንታ አንዱ ነው።

የ34 ዓመቱ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን አምበል፤ በቀጣዮቹ ቀናት ውሉ ይጠናቀቃልና በነፃ ዝውውር ሊቨርፑልን በይፋ ይለቃል።

ሳላህ በአንፊልድ ባሳለፋቸው 9 ድንቅ ዓመታት ውስጥ ራሱን በክለቡ ታሪክ ውስጥ ካለፉ ታላላቅ ተጫዋቾች ተርታ ያሰለፈ ሲሆን፣ ለክለብና ለሀገሩ ከ300 በላይ ግቦችን አስቆጥሯል።

ሊቨርፑል የፕሪሚየር ሊግ፣ የሻምፒዮንስ ሊግ፣ የኤፍኤ እና ሌሎች ዋንጫዎችን እንዲያነሳም ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

የውድድር ዘመኑ መዝጊያ ላይ በእንባ የታጀበ ስንብት ማድረጉን ተከትሎ፣ በድጋሚ በሊቨርፑል መለያ የመታየት ዕድሉ እንዲሁም በሌላ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ውስጥ የመጫወት ተስፋው እጅግ በጣም ጠባብ መሆኑ ሲገለፅ ቆይቷል።

ዕድሜው 34 ቢደርስም አሁንም በዓለም እግር ኳስ ውስጥ በጥብቅ ከሚፈለጉ ክዋክብት አንዱ የሆነው ሳላህ፣ አራት ዋና ዋና አማራጮች ከፊቱ ተደቅነዋል።

እንደ ቅርቦቹ ዓመታት በርካታ ረብጣ ሚሊዮኖችን አፍስሰው ውድ ኮከቦችን ወደ ሊጋቸው መውሰድ ልምድ ያደረጉት የሳዑዲ ክለቦች፤ ይህንን የአንፊልድ ትዝታ ኮከብ በእጃቸው ለማስገባት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ይህ ቀዳሚው የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ ጉዳይ ነው።

የቱርኪዬው ግዙፍ ክለብ ፌነርባቼም የሳላህን ሁኔታ በቅርብ ከሚከታተሉት መካከል አንዱ ነው። ሳላህ የሳዑዲን ያክልም ባይሆን ኮከቦችን በሚቀላቅለው የቱርኪዬ ሊግ ሊታይ ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ አይሆንም ተብሎ የተዘጋ አይደለም።

በጣልያን ያሉ አንዳንድ ክለቦችም ተጫዋቹን በነፃ ለማስፈረም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ሊዮኔል ሜሲን ጨምሮ ታላላቅ ከዋክብትን የሰበሰበው የአሜሪካው ሜጀር ሊግም፣ የሳላህ ማረፊያ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ የዘመናዊ እግር ኳስ ሌላኛው የስበት ማዕከል ነው።

ይህ ሁሉ የዝውውር የቢሆን መላ ምት ከሜዳ ውጪ ቢናፈስም፣ ሳላህ ግን ሙሉ ትኩረቱን ዓለም ዋንጫው ላይ አድርጓል።

ግብፅ ኒውዚላንድን 3 ለ 1 አሸንፋ በታሪኳ የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ ድል ስታስመዘግብ እርሱ አንድ ግብ እና አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።

አሁን ደግሞ በ92 ዓመታት የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪካቸው አዲስ ምዕራፍ በገለጡበት የአሜሪካው ውድድር፤ ብሔራዊ ቡድኑን ይዞ ወደ ጥሎ ማለፍ በመግባት አዲስ ታሪክ ለመጻፍ እየተዘጋጀ ይገኛል።

በእሱባለው ተሾመ