Search

ብራዚል ያነባች ዕለት - የጀርመኑ ዓለም ዋንጫ ትዝታዎች

ማክሰኞ ሰኔ 23, 2018 75

ያኔ ብራዚል እንዲህ ትሆናለች፣ በመሰል ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለው ብዙዎች አልጠበቁም። ሁለት አስርት ዓመታት አልፈው ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያስታውሱት የሆነው ግን እንደዚያ ነው። የ2006 ዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ የቀደመውን አሸናፊ ፈረንሳይ እና የወቅቱን  ሻምፒዮን ብራዚልን አገናኝቷል።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የብራዚል ወርቃማ ትውልድ፣ ኳስ የጥበብ አውድማ መሆኑን ዳግም ያስመሰከሩት ጥበበኞች ስብስብ ጀርመን ምድር ለዓለም ዋንጫው ሲዘልቁ ለ6ኛ የመድረኩ አሸናፊነት፣ ለተከታታይ ሻፒዮንነት ነው የታጩት።

ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ ዴሊማ፣ ሮናልዲንሆ ጎቾ፣ ካካ፣ ካፉ፣ ሮቤርቶ ካርሎስ፣ አድሪያኖ እና ዚ ሮቤርቶን የመሰሉ ክዋክብት እንደ ምን ይዘነጋሉ? የሰው አዕምሮ ሊዘነጋቸው ቢፈቅድ እንኳ የእግር ኳስ ታሪክ ሊረሳቸው አይቻለውም። ትዝታቸው ርቆ ያልራቀ፣ ደብዝዞ ያልጠፋ፣ ቀጥኖ ያልተበጠሰ ህልው ነው። ከመዘንጋት የራቀ ታሪክ!

የዚያች ዕለት ግን ቀን ከነርሱ በተቃራኒ የቆመች መሰለች። የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በተለይም ዚነዲን ዚዳን በዚያች ቀን ስል፣ አስፈሪ እና ባለ ግርማ ሞገስ ሆነው ነው የቀረቡት።

ዚዳን ፀጉሩ እንደከዳው፣ የጎልማሳነት ደጃፉ ላይ እንደቆመ፣ ከእግር ኳስ የመሰናበቻ ቀናቱ እንደደረሰ ሳይሆን የ20ዎቹ አጋማሽ ላይ እንደሚገኝ ወጣት ነበር ይቦርቅ የነበረው።

በዚያ ጨዋታ ዚዳን የነበረው እንቅስቃሴ በዓለም ዋንጫ ታሪክ በግለሰብ ደረጃ ከተደረጉ እንቅስቃሴዎች ምርጡ እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው። የዘመን ተጋሪው ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ ዴሊማም ያን ጨዋታ አስመልክቶ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ “በዚያ ጨዋታ ዚዳን ያደረገው እንቅስቃሴ ያለማወላዳት በዓለም ዋንጫው ታሪክ ከታዩ ምርጥ ብቃቶች እንደ አንዱ ሊመደብ የተገባ ነው” ነበር ያለው።

ፈረንሳይ በቴሪ ሄንሪ አማካኝነት ባስቆጠረችው ግብ ጨዋታውን 1 ለ 0 አሸንፋ የወቅቱን የዓለም ሻምፒዮን ከውድድሩ አሰናበተቻት። ያኔ ብዙ አለማመኖች ነበሩ፣ የሆነው ከብዙዎቹ ጥበቃ በተቃራኒ ነው።

የ1998 ዓለም ዋንጫ አሸናፊ፣ የነ ዚነዲን ዚዳን ሀገር የወቅቱን የዓለም ሻምፒዮን ከዓለም ዋንጫ አስወጣቻት የሚለው በመጨረሻ የዳኛውን ፊሽካ ተከትሎ የተሰማው ዜና ነበር።

ያ ታሪክ በፍራንክፈርቱ ባልድ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ብቻ ተፈፅሞ ያበቃ አልሆነም። ወደ ካናሪንሀ መልበሻ ክፍልም ተከትሎ አምርቷል። በዕለቱ ልዩ የነበረው፣ ለቴሪ ሄንሪም ለግብ የምትሆነውን ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ዚነዲን ዚዳን ወደዚያች መልበሻ ክፍል አመራ።

አንድም ሊያፅናና አንድም በትልልቅ የእግር ኳስ መድረኮች እንደተለመደው መለያ ሊቀያየር።

ኤል ፌኖሜኖ’ ይህን የዚዳን ተግባር በበጎ አልተመከተውም። ሮናልዶ ከ20 ዓመታት በኋላ ሁነቱን አስመልክቶ ሲናገር “ሁላችንም ዛሬ ድረስ አብረን የቀጠልን ጓደኛሞች ነን፣ እርሱ ወደ መልበሻ ክፍል ሲገባ ግን የነበረው ድባብ አስፈሪ ነበር።

ብዙ ተጫዋቾች እያነቡ ነበር፤ እናም መለያ ለመቀያየር ወደ መልበሻ ክፍሉ የመጣበት ሰዓት ትክክለኛ እንዳልሆነና እንዲመለስ አስረግጬ ነገርኩት” ይላል።

እንደ ሮናልዶ እምነት ያች ዕለት የዓለም ዋንጫን ታሪክ ራሱን ቀይራለች። በእርግጥም በብራዚል በኩል ሆኖ ለተመለከተው ብዙ እውነት የሚመስሉ ነገሮችን የያዘ ሃሳብ ነው።

ለዓለም እግር ኳስ የስኬታማነት ናሙና የሆኑ ክዋክብትን ያበረከተችው ብራዚል ከትልቁ መድረክ አሸናፊነት እንደተናጠበች ሩብ ምዕተ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው። እነዛን ኮከቦች ግን እግር ኳስ ሊዘነጋቸው አይቻለውም።

በእርግጥ ፈረንሳይ አስከ ፍፃሜ ብትጓዝም፣ በዚነዲን ዚዳን እና ማርኮ ማታራዚ ድራማ በታጀበው ጨዋታ፣ በነ ማርሴሎ ሊፒ እና አንድሪያ ፒርሎ ጣሊያን ተረታ ለሌላ ዓለም ዋንጫ አሸናፊነት 12 ዓመታት ለመጠበቅ ተገዳለች።

ዚዳንን የ2006ቱ ዓለም ዋንጫ አንተ በእግር ኳስ ስንብትህ ደጃፍ ላይ ቆመህ በእኔ ያበራህ ኮከብ ነህ’ ብሎታል።

ዓለም ዋንጫ ትዝታ ነው። ድልና ሽንፈት፣ ደስታ እና ሀዘን፣ ሳቅ እና ለቅሶ የሚመላለስበት የስፖርት አውድማ፤ የትውስታ መቼት ነው። መንገዱ ይቀጥላል!

በእድሪስ አህመድ