ኮሚቴው የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ንረት በሀገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት ላይ የሚያሳድረውን ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመካከለኛ ጊዜ ለማሳካት የያዘውን የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት ዓላማ ለማሳካት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ግንዘቤ ወስዷል፡፡
በዚሁም መሠረት፣ ኮሚቴው የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ገደብን (credit cap) ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም በወለድ ምጣኔ ላይ ተመስርቶ ወደሚሰራ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እስኪሸጋገር ድረስ በጊዜያዊነት ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የብድር ገደቡ የታቀደለትን ዓላማ ያሳካ በመሆኑ፣ ኮሚቴው ገደቡ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ምክረ ሐሳብ አቅርቦ ቦርዱም አጽድቋል፡፡
ነገር ግን ይህ የብድር ገደብ መነሳት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ለውጥ ሳይሆን፣ የወለድ ተመንን መሠረት ያደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ወደ ተሳካ ሽግግር በመድረሱና ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ውጤታማ እየሆነ በመምጣታቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን ለማስቀጠል በፖሊሲ ማዕቀፉ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን መጠቀሙን ይቀጥላል፡፡
ኮሚቴው የብድር ዕድገት ገደብ መነሳትን ተከትሎ ተመጣጣኝ የሆነ የጥብቅ ፖሊሲ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግ መሆኑን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመገንዘቡ፣ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔን በ1.0 መቶኛ ነጥብ (ከ15 በመቶ ወደ 16 በመቶ) ለማሳደግ እና የ + 3 የመቶኛ ነጥብ ክልል (band) ሳይለወጥ እንዲቆይ ምክረ ሃሳብ አቅርቦ በቦርዱ ጸድቋል።
የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያካሂደው መደበኛ ግምገማ መሠረት የእያንዳንዱ ባንክ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ ጥመርታ (loan-to-deposit ratio) ላይ በመመርኮዝ የተለየ የመጠባበቂያ ተቀማጭ (targeted reserve requirement) እንዲተገብር ኮሚቴው ምክረ ሐሳብ አቅርቦ በቦርዱ ጸድቋል፡፡
ከሸቀጦች ገቢ ንግድ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የዋጋ ግሽበት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመገደብ እና የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ኮሚሽን ምጣኔ ከ2.5 በመቶ ወደ 1.5 በመቶ (በ1 የመቶኛ ነጥብ) እንዲቀንስ ምክረ ሐሳብ አቅርቦ በቦርዱ ጸድቋል፡፡
የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል፣ የገበያ ላይ መተማመን ለመገንባት እና የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማሳለጥ፣ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ለባንኮች እንዲሸጡ የሚጠየቀው 50 በመቶ (FX surrender requirement) ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲደረግ ኮሚቴው ምክረ ሐሳብ አቅርቦ በቦርዱ ጸድቋል፡፡
ኮሚቴው በመስከረም 2019 ዓ.ም መጨረሻ እንደገና ለመሰብሰብ፣ አስፈላጊ ሁኔታ ከተፈጠረም ከዚያ ቀደም ብሎ ለመሰብሰብ ተስማምቷል፡፡
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: