ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባህልና በተፈጥሮ ሀብት የታደለች፣ የበርካታ የዓለም ቅርሶች ባለቤት የሆነች ሀገር ናት። ይሁን እንጂ ይህን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም ከመቀየር አንጻር ዘርፉ ለብዙ ዓመታት በርካታ ተግዳሮቶች ሲገጥሙት ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ግን፣ የመደመር መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ አሮጌውን አካሄድ በመቀየር፣ በአዳዲስ ስትራቴጂዎችና ሜጋ ፕሮጀክቶች የታገዘ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ቱሪዝም በአብዛኛው የታሪክና የሃይማኖት ቅርሶችን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነበር። አሁን ላይ ይህ አካሄድ ተቀይሮ የቱሪስት መዳረሻዎች ብዝኃነትን እንዲያካትቱ ተደርጓል።
በአዲስ አበባ በ“ገበታ ለሸገር” ፕሮጀክት የተገነቡት እንደ አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የወዳጅነት አደባባይ ያሉ ፕሮጀክቶች ዋና ከተማዋን የቱሪስት ማረፊያና መስኅብ አድርገዋታል።
አንዲሁም በገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተገነቡት የቱሪዝም መስኅቦች የሀገራችን የተፈጥሮ ውበት እና ሥነ-ምህዳር ለዓለም አቀፍ ጎብኝዎች በአዲስ መልክ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል የቱሪዝም ዕድገት ያለ አስተማማኝ መሠረተ-ልማት ሊታሰብ የማይችል ሲሆን፣ በዚህ ረገድ የተሠሩ ሥራዎችም ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በመጨመር እና የአውሮፕላን ማረፊያ መሠረተ-ልማቶችን በሀገር ውስጥ በማስፋፋት ተጓዦችን ከዓለም ዙሪያ በቀላሉ የማገናኘት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
በተጨማሪም የኢ-ቪዛ አሰጣጥ መዘርጋት እና የኦንላይን የክፍያ ሥርዓቶች መዘመን የጎብኝዎችን እንግልት በመቀነስ የጉዞ ሂደቱን ቀላልና ፈጣን በማድረግ ሀገራችን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እያስቻላት ነው።
የቱሪዝም ዕድገት ስትራቴጂ ትኩረት የነዋሪውን ማኅበረሰብ ሕይወት መለወጥ ላይ ነው። በአዳዲስ መዳረሻዎች አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በዕደ-ጥበብ፣ በቅርስ ጥበቃ፣ በሎጅና በእንግዳ ተቀባይነት ዘርፍ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። ይህም ቅርሶችና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠበቁ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ካለበት "የማይነካ እምቅ አቅም" ተሻግሮ ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ ምሰሶነት እየተቀየረ ይገኛል። አዳዲስ መዳረሻዎችን ማልማት፣ ጥራትን ማሻሻል እና ዲጂታል ስትራቴጂዎችን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ፣ ቱሪዝም ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ቀዳሚው አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑ አይቀሬ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: