የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን በተመለከተ ባካሄደው ግምገማዊ ውይይት ጠንካራና የተረጋጋ ሀገረ-መንግሥት ለመፍጠር በሚያግዝ መልኩ የተሳካ ስምሪት ማድረጉን ገልጿል።
በ2018 በጀት አመት መጀመሪያ ዓለም አቀፋዊ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት በመገንዘብና ስጋቶችን አስቀድሞ በመተንተን ወደ ተግባር መገባቱን የጠቆመው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፤ በተለይ የ7ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ደኅንነት ማዕከል በማድረግ የተዘጋጀውን የበጀት ዓመቱን ቁልፍ ግብ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በማሳከት የጸና ሀገረ-መንግሥት የመገንባት ሂደቱ ላይ ጉልህ ሚና መጫወት መቻሉን ጠቁሟል።
ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሞች መከበርና ማደግ እንዲሁም ለዜጎች ደኅንነት ስጋት በሆኑ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ወቅታዊ መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶች በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ለውሳኔ ሰጪ አካላትና ለኦፕሬሽናል ግዳጆች ማዋል መቻሉ በመግለጫው ተመላክቷል። በዚህም የሽብርና ታጣቂ ቡድኖችን የመረጃ፣ የሎጀስቲክስ እና የሽብር መረብ በመበጣጠስና ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማካሄድ እንደ ሀገር ተደቅነው የነበሩ በርካታ ስጋቶችን ማክሸፍ መቻሉን አስታውቋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ያስገኛቸውን ጥቅሞች በሚጻረር መልኩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችንና የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመከላከል የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በተከናወኑ የመረጃ ስምሪቶችና ኦፕሬሽኖች በርካታ በሕገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ ሰዎች ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉም በመግለጫው ተጠቅሷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በውጭ መረጃ ስምሪቱ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች በላቀ ደረጃ የሚያረጋግጡ ስኬቶችን ማስመዝገቡን መግለጫው ጠቅሷል። በዚህ ረገድ በቀጣናው እና በዓለም-አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ የኃይል አሰላለፍ ለውጦችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ አዝማሚያዎችን በመረዳትና በመተንተን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት፣ ጥቅምና ክብር የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎች ለመከተል የሚያግዙ ስትራቴጂካል መረጃዎች መሰብሰብና ማሰራጨት መቻሉና ተጨባጭ ለውጥ መገኘቱንም አስታውቋል።
ከውጭ አቻ ተቋማት ጋር መርህን በጠበቀ መልኩ የተከናወኑ የአጋርነትና ትብብር ሥራዎችም ሽብርተኝነትን፤ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ሕገ-ወጥ የገንዘብና የጦር-መሣሪያ ዝውውሮችን በመከላከል ከፍተኛ ሚና እንዳበረከቱ አመልክቷል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ በደኅንነት ስምሪት ማዕቀፉ፤ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማትን፤ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ስልታዊ መሰረተ-ልማቶችን እና ታላላቅ ሀገራዊ ኹነቶችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የመጠበቅ አቅም እንደገነባ በመግለጫው ተጠቁሟል። አስተማማኝ በሆነ መንገድ በቴክኖሎጂ ጭምር ታግዞ የተገነባው ደኅንነትን የማረጋገጥ ስርዓት ኢትዮጵያ ተመራጭ የኮንፈረስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እገዛ ማድረጉም ተገልጿል።
የአቪዬሽን ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ የተከናወኑ ሥራዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝና ተመራጭ እንዲሆን የራሱን አስተዋጽዖ እያደረገ መቀጠሉ በዓመታዊ ግምገማው ተነስቷል። በበጀት አመቱ ይህን ስኬት በአሠራርና በቴክኖሎጂ ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትም ስኬታማ እንደነበሩ ተመላክቷል። የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅትና የሌሎችም ምዘና ተቋማትን ኦዲቶችን ያለምንም ጉድለት ማጠናቀቅ መቻሉና የአቪዬሽን ደኅንነት አዋጅ ተሻሽሎ መጽደቁም በአብነት የሚጠቀሱ ስኬቶች መሆናቸው ተረጋግጧል።
እንደ ሀገር የሚቃጡ የሥነ-ልቦና ጦርነቶችን ለመመከትና ለማጥቃት በተሰጡት የማስተባበር ሥራዎች ከጠላት ኃይሎች የሚቃጡ ሙከራዎችን ከማክሸፍ ባሻገር፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሕብረትን የሚያፀኑ እንዲሁም የኢትዮጵያን ገፅታ የሚገነቡ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል።
በበጀት ዓመቱ ለመረጃ፣ ለደኅንነትና ለሥነ-ልቦና ጦርነት ስምሪት የሚውሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም በማበልፀግ የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ የተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸው መገምገሙ ተመላክቷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ እንዳመለከተው፤ በቀጣይ የላቀ አፈጻጸም ያለው ተቋም ለመገንባት የሚከናወኑትን ሥራዎች ለማጠናከር ሪፎርሙን በአዳዲስ ዕይታዎች የሚያበለፅጉ አቅጣጫዎች ተቀምጧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: