ኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂ የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የመልክዓ ምድር እና እምቅ የባህል ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም፣ እነዚህን ጸጋዎች አቀናጅቶ እና አልምቶ ለመጠቀም የሚያስችል ሥልታዊ ዕቅድ እና ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ለዘመናት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጨባጭ አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ ቆይተዋል።
ነገር ግን ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በሀገራችን ተግባራዊ የተደረጉት ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች ይህንን የአስተሳሰብ አጥር በመስበር፣ የሀገራችንን እውነተኛ አቅም ወደ መግለጥ ተሸጋግረዋል።
ይህ ስኬት የመጣው የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍ፣ የማኅበረሰቡን እና የተፈጥሮን አቅም በአንድ የጋራ ሕልም ዙሪያ አስተባብሮ ከሚመራው የመደመር ፍልስፍና ነው። ዜጎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ እንዲወዱ እና እንዲኮሩባት የተደረገው ብሔራዊ ጥሪ ቱሪዝምን ከተለመደው የታሪክ ጥበቃ አልፎ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሞተርነት አሸጋግሮታል።
በቱሪዝም ዘርፍ የታየው ይህ ሥር ነቀል ለውጥ የመጣው ታዲያ ፈጣን እና ፈጠራ በተሞላበት የፕሮጀክት አመራር የተመራ ሥልታዊ ለውጥ ነው። ይህ ጉዞ በ2011 ዓ.ም አዲስ አበባን ለማስዋብ ከተጀመረው እና እንጦጦ እንዲሁም ሸገር ፓርኮችን እውን ካደረገው "ገበታ ለሸገር" መርሐ ግብር ጅማሮውን አድርጓል።
የዚህ ፕሮጀክት መሳካት በ2012 ዓ.ም ልማቱን ወደ ክልሎች በማስፋፋት በጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ የተፈጥሮ መዳረሻዎችን በከፍተኛ ጥራት ያለማውን "ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክትን ወልዷል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ስምንት አዳዲስ መዳረሻዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለማው "ገበታ ለትውልድ" መርሐ ግብር ሀገራዊ የቱሪዝም ገጽታን በመሠረታዊነት እየቀየረ ይገኛል።
የእነዚህን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎች አስተዳደር ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ለተመረጡ ባለሀብቶች መሰጠቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ ሥልታዊ ድልድይ ሆኗል።
በእነዚህ መርሐ ግብሮች የተገነቡት ፕሮጀክቶች የመደመር እሳቤን በተግባር የሚያሳዩ ተጨባጭ የልማት ዕንቁዎች ናቸው።
በደቡብ ኢትዮጵያ የተመረቀው የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ከአዲስ አበባ ውጪ በማስፋፋት እና ከአባያ እንዲሁም ጫሞ ሐይቆች ተፈጥሯዊ ውበት ጋር በመዋሃድ ለአካባቢው ኢኮኖሚ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት 13.3 ሔክታር ላይ ያረፈ ዘመናዊ መገልገያዎችን እና የሔሊኮፕተር ማረፊያን ያካተተ ሲሆን፣ የሰሜኑን የሀገራችን የቱሪስት መስመር የሚያስተሳስር ወሳኝ ማዕከል ሆኗል።
በአፋር ክልል የተገነባው የኒዒን ሌ ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ጋር ባለው ቅርበት የተፈጥሮ ፍል ውኃን እና ሐይቅን በማቀናጀት የቱሪዝም አቅምን እያጎላ ይገኛል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተገነባው ደንቢ ኢኮ ሎጅ በበካ የቡና እርሻ አጠገብ ሙሉ በሙሉ ከአካባቢው የተገኙ የተፈጥሮ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የተገነባ የዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሞዴል ነው። በዚሁ ክልል የሚገኘው የሀላላ ኬላ ሪዞርትም በጊቤ ሦስት ሰው ሠራሽ ሐይቅ ዳርቻ የተገነባ ሌላው አስደናቂ ማሳያ ነው።
እነዚህ ታላላቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች በማክሮ ኢኮኖሚክስ ዕይታ የቱሪዝምን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በከፍተኛ ደረጃ የሚያባዙ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ቁሳቁሶች እና በኢትዮጵያውያን አቅም መገንባታቸው በአካባቢው ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጠረውን የግብይት ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ይህ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ከያዘችው ግብ ጋር በቀጥታ የሚጣጣም ሲሆን፣ ዘንድሮ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ5.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ የዚህ የመደመር ቀመር ተግባራዊ ስኬት ነው።
የገበታ መርሐ ግብሮች ከተለመደው የቢሮክራሲ አሠራር ወጥተው በፈጠራ የታገዘ የፕሮጀክት አመራርን በማሳየት፣ የኢትዮጵያን የተዳፈነ ጸጋ ወደ ተግባራዊ ሀብት በመቀየር ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ሀገርን ለማስረከብ የተጀመረው ጉዞ ስኬታማ ማሳያዎች ናቸው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: