Search

ከ40 ሀገራት ጥያቄ ጀርባ ያለው የብሪክስ+ ሚስጥር እና የኢትዮጵያ አዲሱ የስትራቴጂ ማዕከልነት

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 67

ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የብሪክስ ስብስብ ከተመሰረተበት የመጀመሪያ ደረጃ የኢኮኖሚ ትስስር ዓላማ አልፎ፣ የዓለም አቀፉን የጂኦ-ፖለቲካ እና የአህጉራዊ ትብብር መዋቅር በከፍተኛ ሁኔታ ወደቀየረ ታላቅ የባለብዙ ወገን እንቅስቃሴነት ተሸጋግሯል።

በአሁኑ ወቅት ወደ 40 የሚጠጉ ሀገራት ስብስቡን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየታቸው፣ የደቡቡ ዓለም የበለጠ አካታች፣ ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ የሆነ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ስርዓት ለመገንባት ያለውን ጽኑ ፍላጎት በግልጽ የሚያንፀባርቅ ነው።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የታየው የዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ ዋና ማሳያ፣ ሀገራት በጋራ ተሳትፎ እና በሉዓላዊ እኩልነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የትብብር መንገድ መከተላቸው ነው።

ብሪክስ ስብስቡን እያሰፋና አዳዲስ አጋርነቶችን እየፈጠረ የመጣበት አካሄድ፣ በንግድ መስመሮች፣ በኃይል ኮሪደሮች፣ በታዳሽ ኃይል እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ ዘላቂ ትብብርን የሚያጎለብት ስትራቴጂካዊ መድረክ እንዲሆን አድርጎታል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ፍላጎት የሚታይበት የዚህ ታሪካዊ ለውጥ አካል መሆኗ በዲፕሎማሲያዊ፣ በሎጂስቲክስ እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ዘላቂ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ያስገኝላታል።

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የሰፊ ህዝብ ባለቤት እንደመሆኗ መጠን፣ አህጉሪቱን ከብሪክስ የንግድ እና የሎጂስቲክስ መዋቅር ጋር የምታገናኝ ዋና ድልድይ ሆና ታገለግላለች።

ይህም የአፍሪካን የልማት አጀንዳዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በትልቁ ለማስደመጥ እና አህጉራዊ የዲፕሎማሲ መሪነቷን የበለጠ ለማጠናከር ታላቅ ዕድል ይፈጥርላታል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የሀገራችን የላቀ የአቪዬሽን አቅም እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አህጉራዊ ትስስርን በፍጥነት የሚያፋጥን በመሆኑ፣ ስብስቡ በምስራቅ አፍሪካ ለሚያደርጋቸው የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያን ዋና የሎጂስቲክስና የንግድ መግቢያ ያደርጋታል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ታዳሽ የኃይል አቅርቦት እና የሎጂስቲክስ አቅም ከብሪክስ አባል ሀገራት የቴክኖሎጂ እና የፋብሪካዎች ሽግግር ጋር ሲጣመር፣ ኢትዮጵያ ከጥሬ እቃ ላኪነት ወጥታ ወደ ቀጠናዊ የአምራችነትና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንድትሸጋገር ትልቅ መዋቅራዊ መሰረት ይጥላል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: