ትላንት በመላው ኢትዮጵያ በተካሄደው ታሪካዊ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በ12 ሰዓታት ውስጥ ለመትከል ካቀደችው 800 ሚሊዮን ችግኝ 805 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አዲስ የዓለም አቀፍ ሥነ ምህዳር ጥበቃ ታሪክ አስመዝግባለች።
ከማለዳው ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የመትከያ ስፍራዎች ወጣቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት የተካሄደው ይህ ታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ተፈጥሮአዊ ህልውና እና ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ ምድር ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጡበት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ካቀደችው በላይ 805 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ባስመዘገበችው በዚህ ታላቅ ስኬት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ መልእክቶችን አስተላልፋለች።
የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በመግለጫዎች እና በኮንፈረንሶች ብቻ ሳይሆን በተግባር መሬት ላይ በሚወርዱ ግዙፍ ሕዝባዊ ሥራዎች መመራት እንዳለበት በተግባር የተደገፈ መሪነቷን አሳይታለች።
በሌላ በኩል ሀገራችን የራሷን የደን ሽፋን ከማሳደግ እና የደረቁ የውኃ አካላትን ከመመለስ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በማካፈል በቀጣናው አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጣለች።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እና በሕዝቧ ንቅናቄ ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነቷን መወጣቷን በመግለጽ የበለፀጉ ሀገራት እና የዓለም አቀፍ አካባቢ ጥበቃ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የገቡትን የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ቃል በተግባር እንዲወጡ በድፍረት እንድትሞግት ትልቅ የዲፕሎማሲ ሞራል እና አቅም ፈጥሮላታል።
ይህ ታሪካዊ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጣለባትን እምነት የሚያጸና ሲሆን፣ ሀገራችን በታላላቅ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤዎች ላይ በዘርፉ ያላትን የላቀ የሞራል ልዕልና እና ተደማጭነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዳግም ያስመሰከረ ነው።
የተመዘገበው 805 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ስኬት የዛሬን የተፈጥሮ ቁስል እያከመ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ እና የዓለምን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ በተግባር የተጻፈ ታሪካዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ምዕራፍ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: