ኢትዮጵያ በታሪኳ ትልቅ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ሀገራችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት፣ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት እና በዋና ዋና ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የዚህ ዘመን ትልቁ ታሪካዊ ክስተት ነው።
እንደ ሀገር የገጠሙንን ዘመናት የተሻገሩ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ውጥንቅጦችን በዘላቂነት ለመፍታት ከግጭት ይልቅ ውይይትን፣ ከመግፋት ይልቅ አሳታፊነትን ማስቀደም ብቸኛው ዘላቂ መንገድ መሆኑ ግልጽ እውነታ ሆኗል።
የሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ዓላማ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቁ እና መፍትሔ ያላገኙ መዋቅራዊ እና ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ማጥበብ ነው። ሕዝቡ በነጻነት አስተያየቱን እንዲሰጥ በማድረግ የጋራ እሴቶችን መቅረጽ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን እና ብዝኃነትን ያጣጣመ የጋራ የወደፊት ራዕይ በመቅረጽ የወል ትርክትን መገንባት ነው።
ይህንን የምክክር ሒደት ልዩ የሚያደርገው ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ውሳኔ ሳይሆን፣ ከታች ወደ ላይ የኅብረተሰቡን ድምፅ የሚሰበስብ መሆኑ ነው። እውነተኛ ሀገር ግንባታ የሚጀምረውም የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ እኩል ዋጋ አግኝቶ ሲደመጥ ብቻ ነው።
የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበራት በተወካዮቻቸው አማካኝነት የአጀንዳ ግብዓት ማቅረባቸው የሒደቱን ተቀባይነት እና ሕጋዊነት በማጎልበት አሳታፊነትን ማረጋገጥ ተችሏል።
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በየክልሎቹ እና በከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች መረጣ ሒደቶችን ባከናወነበት ወቅት ሒደቱ ግልጽነት ያለው እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲሄድ ማድረጉ ለምክክሩ ተዓማኒነት የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የትውልድ አደራ እና የጠንካራ ሀገር ግንባታ መሠረት ሲሆን፣ የዚህ ጉባኤ ስኬት የሚወሰነውም በኮሚሽኑ ጥረት ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዳችን በጎ ፈቃድ፣ አዳምጦ የመረዳት ባህል እና ለሀገራዊ አንድነት በምናሳየው ቁርጠኝነት ነው።
ውጤታማ ምክክር ያደረጉ ሀገራት ከቀውስ ወጥተው ወደ ብልጽግና እንደተሸጋገሩ ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በዚሁ መንገድ በሰላም፣ በእኩልነት እና በብልጽግና ላይ የተመሠረተች ሀገር ሆና እንደምትቀጥል እምነታችን የጸና ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: