76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ስብሰባ (RC76) ከነሐሴ 18 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ስብሰባው ከዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ነው።
በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና መረጃ መሠረት፣ ስብስባው የቀጣናውን የጤና አጀንዳዎች ላይ መምከር እና አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነው።
የ47ቱ የአፍሪካ ቀጣና አባል ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የዓለም አቀፍ ጤና መሪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ ለጋሾች እና የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮችን ጨምሮ ከ600 በላይ ተወካዮች በስብስባው ላይ ይሳተፋሉ።
የስብሰባው ተሳታፊዎች በቀጣናዊ የጤና አቅዶች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚገመግሙ ሲሆን በአዳዲስ ስትራቴጂዎች እና የውሳኔ ሐሳቦች ላይ ይመክራሉ።
እንዲሁም የጤና ሥርዓቶችን ለማጠናከር፣ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ የጤና ደኅንነትን ለማሻሻል እና የአደጋ ጊዜ ዝግጁነትን ለማሳደግ የሚረዱ የጋራ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ፤ ስብሰባው አባል ሀገራት የቀጣናውን የጤና አጀንዳ እንዲቀርጹ፣ አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ እና በመላው አፍሪካ ጤናማ፣ አስተማማኝ እና ጠንካራ ማኅበረሰቦችን የመገንባት ሂደት ለማፋጠን ትልቅ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ተወካዩ አክለውም የኢትዮጵያ ስብሰባውን ማስተናገድ፣ ለቀጣናዊ ወንድማማችነት እና ለጋራ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ አህጉራዊ ጉባኤ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ስኬቶች፣ በተለይም መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በማስፋፋት ሌሎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማሳየት ዕድል እንደሚፈጥር መረጃው አመልክቷል።
ስብስባው የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ፣ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በመጠቀም ለጋራ የጤና ፈተናዎች የተቀናጀ አህጉራዊ ምላሽ ለመስጠት ስትራቴጂያዊ መድረክ እንድትሆን ያደርጋታል።
በስብስባው ላይ የቴክኒክ ውይይቶች፣ አውደ ርዕዮች፣ የሁለትዮሽ ስብሰባዎች እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች የሚካሄዱ ሲሆን፣ እነዚህም በአፍሪካ ተቋማት መካከል የጤናው ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎችን እና የእውቀት ልውውጥን የሚያጎሉ እንደሚሆኑ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ የቀጣናዊ ጽሕፈት ቤቱ የበላይ አካል ሲሆን፤ በየዓመቱ በመሰብሰብ የቀጣናውን የጤና ፖሊሲ ይወስናል፣ የድርጅቱን ሥራዎች ይገመግማል፣ እንዲሁም በመላው አህጉሪቱ ለሚከናወኑ የጤና ተግባራት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አጀንዳዎች ያስቀምጣል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: