የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ጉባኤ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ያስመዘገቡት ታላቅ ድል የሚያስደስት መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ የሁሉም ወገን ድምፅ የተሰማበት መሆኑን የጠቆሙት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ለሀገራዊ መግባባት ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ምንጊዜም የታሪክ የማዕዘን ድንጋይ መሆኗን አንሥተው፣ በዓድዋ ያበራችው የነጻነት ችቦ ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓድዋ ድል የጦር ሜዳ ስኬት ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ ክብርን ያጎናጸፈ እና በኢትዮጵያውያን ኅብር የተገኘ የአንድነት ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በሊግ ኦፍ ኔሽንስ የተደረገው ታሪካዊ ንግግር የዓለምን ታሪክ የቀየረ እና ለአፍሪካ ኅብረት ብርሃን የፈነጠቀ እንደነበር በማስታወስ፣ ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ነጻነት እና አንድነት ፋና ወጊ መሆኗን መስክረዋል።
ኡሁሩ ኬንያታ የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊነት ሲገልጹ፣ ኢትዮጵያ በኅብር ቀለም የተጋመደች ውበት መሆኗን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ታላቅነት መሠረቱ ይኸው ኅብረ ብሔራዊነቷ መሆኑን በመጠቆም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውም ወገን ለብቻው ተነጥሎ ድል ማምጣት እንደማይችል አስረድተዋል።
ለኢትዮጵያ ጉዳይ ማንም የውጭ አካል የሚወስን ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን እና ታሪካቸው ብቻ ወሳኝ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉንም ሕዝቧን የምትፈልግ መሆኗን የገለጹት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን እንደገና እየጻፉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዓለም ላይ የሐሳብ ልዩነት እና ግጭት የሌለበት ቦታ እንደሌለ በማንሳት፣ ዋናው ልዩነት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በውይይት መፍትሔ በመፈለግ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አብራርተዋል። በንግግራቸው ማጠቃለያም የቆሙበት ቦታ የቆየ ታሪክ መሆኑን በመግለጽ፣ ሁልጊዜም ለታላቋ ኢትዮጵያ ሰላም እንደሚያስቡና እንደሚጸልዩ አረጋግጠዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: