ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ በርካታ ውጣ ውረዶችን፣ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን እና የርስ በርስ ግጭቶችን አስተናግዳለች።
ይሁን እንጂ፣ ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስንመለከት፣ ሀገራችን የልዩነቶቿን እና የዘመናት የታሪክ ስብራቶቿን በጥበብ፣ በሠለጠነ ውይይት እና በጋራ መደማመጥ የጠገነችበት ታሪካዊ ምዕራፍ አስመዝግባለች።
ይህ በሀገራችን ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ የመጀመሪያው እና ውጤታማ የነበረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት፣ ከማዕዘናት እስከ ማዕዘናት የተሰማውን የሕዝብ ድምፅ አስተባብሮ በሙሉ ስኬት ተጠናቅቋል።
የጠረጴዛ ዙሪያ ፖለቲካ እና የመደመር ፍልስፍና
ለዘመናት የዘለቀው የኃይል እና የግጭት መንገድ አብቅቶ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ የመነጋገር እና የመደማመጥ ባህል የበላይነት ያገኘበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
ይህ ክስተት የፖለቲካ ምኅዳራችንን ወደ አዲስ የመደመር እና የጽኑ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ምዕራፍ ያሸጋገረ ታሪካዊ እመርታ ነው። ልዩነቶችን በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሠለጠነ የሐሳብ ልውውጥ መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያየንበት፣ ዴሞክራሲያዊ ባህላችን እያበበ መምጣቱን ያረጋገጠ ሂደት ነው።
በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ከቀረቡት ከ400 በላይ ከሆኑ ዐበይት፣ ውስብስብ እና ለዘመናት ከተከማቹ ሀገራዊ አጀንዳዎች መካከል 99% ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱ የመድረኩን ጥበብ እና ታላቅነት በግልጽ ያሳያል።
ከታች ወደ ላይ፡ የእውነተኛ አሳታፊነት ማሳያ
ይህ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬታማ ሊሆን የቻለው፣ ከታች ከንዑስ የቡድን ውይይት ጀምሮ እስከ ትልቁ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ድረስ ባደረገው ጥልቅ፣ ግልጽ እና አሳታፊ አወቃቀሩ ነው።
የሕዝብን እውነተኛ ፍላጎት ማዕከል በማድረግ፣ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ድምጽ ለማካተት የተደረገው ጥረት ፍሬ አፍርቷል። 99 በመቶ በሚሆኑት አጀንዳዎች ላይ ስምምነት ላይ መደረሱ፣ ኢትዮጵያውያን በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን የጋራ ራዕይ እና አንድነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
የፅንፈኝነት ትርክቶችን ማክሸፍ
ማንኛውም ታላቅ ሀገራዊ ለውጥ ፈተናዎች አይጠፉትም። በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ከመጀመርያው አንሥቶ በፅንፈኛ ኃይሎች እና እውነትን በማደብዘዝ ላይ በተሰማሩ አካላት የተከፈተበት የውንጀላ፣ የሐሰት መረጃ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ቀላል አልነበረም።
ሆኖም፣ ሂደቱ በከፍተኛ ሕዝባዊ አሳታፊነቱ እና ባስመዘገበው ተጨባጭ ውጤት እነዚህን አፍራሽ ትርክቶች ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ ችሏል። የሕዝብ እውነት እና የሰላም ፍላጎት ከማንኛውም የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በላይ ገዝፎ ታይቷል።
ብሩህ ሀገራዊ ተስፋ እና የትውልድ አደራ
ይህ ሀገራዊ ስኬት ሀገረ-መንግሥት ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚጠናቀቅ ሳይሆን የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት መሆኑን ያረጋገጠ ነው። የመደመር መንግሥት የመግባባት ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ የያዘውን ጽኑ ዓላማ በተግባር አስመስክሯል።
ልዩነቶችን በሠለጠነ ውይይት መፍታት እንደሚቻል ማሳየቱ፣ የፖለቲካ ባህላችንን ከግጭት እና ከስሜታዊነት ወደ ማመዛዘን እና ወደ ሀገራዊ መግባባት ያሸጋገረ ታላቅ ድል ነው።
በመሆኑም ሙሉ ሀገራዊ አቅማችንን አስተባብረን እና በፅኑ ስሜት ተሰልፈን ሂደቱን በስኬት ማጠናቀቃችን "ኢትዮጵያ አሸንፋለች" የሚለውን ሐሳብ በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ኢትዮጵያ ያሸነፈችው የብጥብጥ እና የልዩነት ድምፆች አብቅተው የውይይት፣ የእርቅ እና የጋራ ስምምነት ባህል የበላይነት በማግኘቱ፤ እንዲሁም ከትንሽ እስከ ትልቅ የሕዝቧ ድምፅ ተሰምቶ ለዘመናት የቆዩ አጀንዳዎች የጋራ ስምምነት ምላሽ በማግኘታቸው ነው።
ይህ የተመዘገበው ሀገራዊ ድል የሁላችንም የጋራ ሀብት ሲሆን፣ ወደፊት ለምናደርገው የልማት እና የዴሞክራሲ ጉዞም ጽኑ መሠረት ጥሏል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: