የኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ መድረሱን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መብራቱ ተሾመ ገለጹ።
201 ሜትር ርዝመት ያለው የግድብ ግንባታው 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የአፈር ቁፋሮ በማካሄድ አጠቃላይ ግድቡ ከሚፈልገው 7 ነጥብ 72 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት ውስጥ 81 ነጥብ 2 በመቶው ማለትም 6 ነጥብ 27 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት (RCC) ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የኃይል ማመንጫ ቤቱ የቁፋሮ ሥራ እንዲሁም የሲቪል ሥራው የመጀመሪያ ደረጃ የኮንክሪት ሙሌት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን በታቀደው ጊዜ ለማጠናቀቅ ዕቃዎች በበርካታ ፋብሪካዎች እንዲመረቱ መደረጉንም ገልጸዋል።
የፋይናንስ አቅርቦት በተለይም የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ተያያዥ ችግሮች በግንባታው ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ መቆየቱን ያስታወሱት ኢንጂነር መብራቱ፣ አሁን ላይ ተቋሙ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በራሱ በመሸፈኑ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል።
የግድብ ግንባታውን በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ እና በጥቅምት 2021 ዓ.ም የመጀመሪያውን ተርባይን ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት እየተሠራ ስለመሆኑም መጠቆማቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: