የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ገጽታ የሚያድሱ፣ የትራንስፖርት መጨናነቅን በዘላቂነት የሚቀርፉ እና ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ከመሬት በታች የተገነቡ ትላልቅና ዘመናዊ የመኪና ፓርኪንግ ፕላዛዎችን እንዲሁም የታክሲ እና የአውቶቡስ ተርሚናሎችን መርቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት አድርጓል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አስተዳደሩ የሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል እና የተገቡ ቃሎችን በተግባር ለማዋል የሚከናወኑ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ቃላችን አንዳንዶች እንደሚሉት ባዶ ፕሮፓጋንዳ እንዳልሆነ ሥራችን ምስክር ነው ብለዋል።
ከጎተራ እስከ ቦሌ፣ ከየካ እስከ ቀበና በአጭር ጊዜ ተገንብተው የተመረቁት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ፈጣን የለውጥ ጉዞ በግልጽ የሚያሳዩ መሆናቸውን አክለዋል።
አዳዲሶቹ ተርሚናሎች ቀደም ሲል እናቶች እና አረጋውያንን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው በከፍተኛ እንግልት እና መገፋፋት ትራንስፖርት ይጠብቁ የነበረበትን አሠራር በመቀየር፤ በክብር አረፍ ብለው ተራቸውን ጠብቀው የሚስተናገዱበት ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችን ብቻ ሳይሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ያካተቱ በመሆናቸው፣ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ራዕይን ለማሳካት ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱም አመላክተዋል።
በተጨማሪም የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የደህንነት ካሜራዎች (CCTV) የተገጠሙላቸው ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ተገናኝቶ የሚወያይባቸውና ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክርባቸው ሰፋፊ ፕላዛዎች፣ ሱቆች እና ካፌዎች በውስጣቸው መያዛቸውን ከንቲባ አዳነች በንግግራቸው አንስተዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በትራንስፖርት ዘርፍ የመጣው ለውጥ መሠረታዊና ታሪካዊ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ቀደም ሲል በከተማዋ የነበረው ከ3 ሺህ ያልበለጠ የመኪና ማቆሚያ አቅም አሁን ላይ ከ180 ሺህ በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
በሥራ እድል ፈጠራ በኩልም በፓርኪንግ ዘርፍ ብቻ እስካሁን ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች ወደ ሥራ መግባታቸውንና አዳዲሶቹ ፕላዛዎች፣ ሱቆችና ካፌዎችም ሰፊ የሥራ ዕድል ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ከዚህ በላይ እንደሚገባት ያመለከቱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ መሠረተ ልማቶቹ ከመሀል ከተማ ወደ ዳርቻዎች እየሰፉ እንደሚሄዱና የትራንስፖርትና ማህበራዊ መስተጋብር ቦታዎችም እያንዳንዱን ሰፈር እንደሚያዳርሱ አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ነዋሪዎች የሕዝብ ሀብት የሆኑትን እነዚህን ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች እንደራሳቸው ንብረት እንዲንከባከቧቸውና እንዲጠብቋቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: