Search

ከአስደናቂ ማሳያ ወደ እውነተኛ የሥራ ዓለም የቻይና ሮቦቶች ዕድገት እና የተደቀኑባቸው ፈተናዎች

ሓሙስ ነሐሴ 21, 2018 238

ቻይና የሰው መልክ ያላቸውን ሮቦቶች (Humanoid Robots) ለማልማትና ለንግድ አጠቃቀም ለማብቃት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የመንግሥት ድጋፍ እያደረገች የምትገኝ ሲሆን ሮቦቲክስን ከወደፊት የኢኮኖሚ እድገቷ ጋር የተያያዘ ቁልፍ ቴክኖሎጂ አድርጋ እያየችው ትገኛለች። 

በቅርቡ በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም የሮቦት ኮንፈረንስ ከ300 በላይ ኩባንያዎች ከ2,000 በላይ የሮቦቲክስ ምርቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከ150 በላይ አዳዲስ ምርቶችም በዝግጅቱ ላይ ተመርቀዋል። 

በዝግጅቱ ወቅት ሮቦቶች ቦክስ፣ እግር ኳስና የጠረንጴዛ ቴኒስ ሲጫወቱ፣ ሙዚቃ ሲያቀነቅኑ፣ በጥቅል የተዘጋጁ ዕቃዎችን ሲለዩና ሲያጓጉዙ እንዲሁም በፋብሪካዎች የሚከናወኑ ተግባራትን ሲፈጽሙ ታይተዋል። 

ሆኖም ግን ከእነዚህ አስደናቂ ማሳያዎች በስተጀርባ ሮቦቶቹ አሁንም በልማት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የሚጠቁሙ ባለሙያዎች፣ በተለይም በእውነተኛ የሥራ አካባቢ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን የመረዳት፣ በራሳቸው ውሳኔ የመስጠትና ተለዋዋጭ ሥራዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ የመፈጸም ጉድለት አሁንም ትልቅ ፈተና እንደሆነ ያመላክታሉ።

ቻይና የሮቦቲክስ ኢንዱስትሪዋን ለማፋጠን የመንግሥት ድጎማን፣ የግብር ማበረታቻዎችንና የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን በስፋት እየተጠቀመች ይገኛለች። 

በ2026 መጀመሪያ ወራት ብቻ ከ230 ሚሊዮን ዶላር በላይ የመንግሥት ድጎማ ለዘርፉ መመደቡ የተገለጸ ሲሆን፣ የቻይና ኩባንያዎችም በዘርፉ ትልቅ የግል ካፒታል እየሳቡ መሆናቸው ይታወቃል። 

ለምሳሌ XPeng የሮቦቲክስ ክፍሉ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቡን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም በቻይና ሮቦቶች ዘርፍ ከተደረጉ ትልልቅ የግል የገንዘብ ማሰባሰቦች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። 

ቻይና በሰው ሰራሽ ሮቦቶች የዓለም ገበያ ላይ ቀዳሚ ለመሆን እየተወዳደረች ቢሆንም፣ ዋናው ፈተና ግን ሮቦቶቹን ከማሳያና ከሙከራ ደረጃ አውጥቶ ወደ ትርፋማና በተግባር ወደሚሰሩ ሥራዎች ማሸጋገር ነው።

ከፍተኛ ዋጋ፣ የተገደበ ችሎታና የእውነተኛ ዓለም መረጃ እጥረት የዘርፉ ዋና ችግሮች ሆነው የቀጠሉ ሲሆን፣ በቅርቡ በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም የሮቦት ጨዋታዎች ላይ ከ2,000 በላይ ሮቦቶች በ51 የውድድር ዘርፎች ተሳትፈዋል። 

በዚህ ውድድር ላይ አንዳንድ ሮቦቶች በሩጫ ከሰው የዓለም ሪከርዶች ጋር የሚወዳደሩ ውጤቶችን ቢያሳዩም፣ በከፍተኛ ፍጥነት ላይ ሚዛናቸውን መቆጣጠርና በደህንነት ማቆም አሁንም ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል። 

በመሆኑም የቻይና ሮቦት ዘርፍ በፍጥነት እየተስፋፋ ቢሆንም፣ ቀጣዩና ወሳኙ እርምጃ አስደናቂ ማሳያዎችን ወደ እውነተኛ የሥራ አቅም፣ የንግድ ትርፍና በስፋት ወደሚጠቀሙባቸው ተግባራዊ ሮቦቶች መቀየር መሆኑን ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ።

በሲሳይ መንግስቱ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: