Search

ከአባይ እስከ ቀይ ባሕር፦ የታሪክ ስብራትን እየጠገነ የመጣው የኢትዮጵያ ጉዞ

ዓርብ ነሐሴ 22, 2018 227

የባሕር በር እና የውኃ ሀብት አጠቃቀም ጉዳይ የኢትዮጵያ የህልውና፣ የብሔራዊ ጥቅም፣ እንዲሁም የዘላቂ እድገት መሠረት እንጂ የጊዜያዊ ፖለቲካ አጀንዳ አይደለም።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት የገጠሟት የታሪክ እና የጂኦግራፊ ስብራቶች እንዳይጠገኑ እንዲሁም የተፈጥሮ መብቷን እንዳታስከብር ማሰናከል የታሪካዊ ባላንጣዎቻችን ዋነኛ ዓላማ ሆኖ ቆይቷል።

እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያውያን ትኩረታቸውን ወደ አባይ እና ቀይ ባሕር እንዳያደርጉ በምትኩ በውስጥ ግጭት እና በመከፋፈል እንዲጠመዱ ሌሊትና ቀን ይሰራሉ።

በተለይም የግብፅ የውኃ ሞኖፖሊ ፍላጎት እና የቀይ ባሕር ቀጣናን አፍኖ የማስቀረት ስትራቴጂክ ሤራ በውስጥ ባንዳዎች ድጋፍ ኢትዮጵያን አሳንሶ ለማስቀረት ያለመ መሆኑ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

ይሁን እንጂ የትኛውም ዓይነት የውጭ ጫና የዲፕሎማሲ አሻጥር ወይም የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ኢትዮጵያውያንን ከቀይ ባሕር እና ከአባይ ወንዝ ብሔራዊ ጥቅማቸው ሊነጥላቸው አይችልም።

በምንም ዓይነት መስዋዕትነት ዓይናችን ከዚህ የሉዓላዊነት አጀንዳ ፈጽሞ አይነቀልም። ይህ የዘመናት የታሪክ በደል የሚታረምበት የፍትህ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር በማጠናከር የሀገራችንን የኢኮኖሚ ነፃነት የሚያረጋግጥ ፅኑ መሠረታችን ነው።

ይህን ታሪካዊ እና ጂኦግራፊያዊ ፍላጎት ከባዶ ምኞት ወደ ተጨባጭ እውነት ለመቀየር የውስጥ ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው ለብሔራዊ ጥቅሙ በአንድነት የሚቆም አዲስ አርበኛ ትውልድ መገንባትን ይጠይቃል።

ይህ አዲስ ትውልድ በጠላት ሤራ የማይበገር፣ የዓባይን ታላቅነት እና የቀይ ባሕርን ስትራቴጂያዊ ወሳኝነት ጠንቅቆ የሚያውቅ የቁርጠኞች ስብስብ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ አስከፊ የሚባሉ ፈተናዎችን በድል ተሻግራለች፤ አሁንም በፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ብሔራዊ ክብሯን አስጠብቃ ቀጥላለች።

ከዓባይ እስከ ቀይ ባሕር የተዘረጋው የጠላቶቻችን ሤራ ቢቀጥልም የኢትዮጵያ የትንሣኤ ጉዞ በፅኑ መሠረት ላይ ተጥሏል።

አጀንዳችን የዚህ አዲስ አርበኛ ትውልድ መሰብሰቢያ እና የብሔራዊ ከፍታችን ማረጋገጫ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: