Search

ከዕለት ጉርስ እስከ አምራችነት፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የፈጠረው ማኅበራዊ አብዮት

ዓርብ ነሐሴ 22, 2018 185

የተራበን ሰው መመገብ እና በችግር ወቅት ደግፎ ማንሳት የኢትዮጵያውያን የቆየ የበጎነት እሴት ነው።

ይሁን እንጂ ዘላቂው የልማት ጥያቄ የሚጀምረው "ከዚያስ በኋላ?" ከሚለው መሠረታዊ ነጥብ ላይ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረው ማኅበራዊ ንቅናቄ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከጊዜያዊ ድጋፍ በማውጣት ዜጎችን ከእርዳታ ጥገኝነት ወደ ዘላቂ አምራችነት የሚያሸጋግር ግዙፍ የለውጥ ኃይል ሆኗል።

የመንግሥት ዋነኛ ግብ የሆነው ተረጂነትን ዜሮ የማድረግ ራዕይም በዚህ አግባብ በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል።

ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የምገባ ማዕከላት የዕለት ፍላጎትን ከመሙላት ባሻገር፣ የዜጎችን ክብር የጠበቀ አዲስ የህይወት ምዕራፍ ፈጥረዋል።

በተለይም በጎዳና ይኖሩ የነበሩ ወጣቶች እና ህፃናትን በማገገሚያ ማዕከላት በማቀፍ የሥነ ልቦና ሕክምና እና የሙያ ክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

ሠልጣኞቹ በተለያዩ ማዕከላት የቀሰሙትን ዕውቀት ከከተማ ግብርና እና ከሌማት ትሩፋት ንቅናቄዎች ጋር በማቀናጀት እንዲሁም በሥራ ፈጠራ እና በፋይናንስ ድጋፍ ታግዘው ራሳቸውን የቻሉ አምራች ዜጎች መሆን ችለዋል።

ድጋፍን ከተሳትፎ፣ ተሳትፎን ደግሞ ራስን ከመቻል ጋር በማስተሳሰር የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብቻ 157.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የወጣቶች አስተዋፅኦ 6.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

በ2017 ዓ.ም በተካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ ዘመቻ ከ23 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ከ57 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

ወጣቶቹ አረንጓዴ ዐሻራቸውን በማሳረፍ፣ ደም በመለገስ እና አረጋውያንን በመንከባከብ ማኅበራዊ ትስስርን እና ሰላምን እያጸኑ ነው።

ሰውን መርዳት በጎነት ቢሆንም፣ ሰውን ማብቃት እና ራሱን እንዲችል ማድረግ ግን የዘላቂ ልማት እና ጠንካራ ማኅበረሰብ ግንባታ መሰረት ነው።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: