Search

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኃይል የማመንጨት አቅሙን 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት አደረሰ

ዓርብ ነሐሴ 22, 2018 225

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ አመርቂ ስኬት በማስመዝገብ አጠቃላይ ሀገራዊ የኃይል ማመንጨት አቅሙን 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት ማድረሱን አስታውቋል።

ተቋሙን ከነበረበት የዓመታት ኪሳራ በማውጣት 39.5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡንም ነው ያስታወቀው።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት አቅጣጫዎችን አስመልከተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ፣ በምርት፣ በሽያጭ እና በገቢ ስብሰባ ረገድ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ታሪካዊ ወቅት እንደነበር ገልጸዋል።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የአይሻ እና የአሰላ የነፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባትና መስፋፋት ሀገራዊ የኃይል ማመንጨት አቅሙ ወደ 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት እንዲያድግ ዋናውን ድርሻ ተጫውተዋል።

በበጀት ዓመቱ ተቋሙ 124.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ከዚህ ቀደም ይደርስበት የነበረውን የፋይናንስ እጥረትና ኪሳራ በመቀየር 92 በመቶ አጠቃላይ አፈጻጸም እንዲመዘገብ አስችሏል።

ከተመረተው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 93.5 በመቶ ያህሉ ለሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ፣ የንግድና የቤት ውስጥ ፍጆታዎች የዋለ ሲሆን፣ ቀሪው 6.5 በመቶ ደግሞ ለጎረቤት ሀገራት በኤክስፖርት ቀርቧል።

ከዚህ የውጭ ሀገር የኃይል ሽያጭ 475.7 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ ይህም አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ብልጫ በማሳየት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በከፍተኛ ደረጃ ደግፏል።

በሒደቱ ወቅት የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም፣ የደኅንነትና የንብረት ሥርቆት እንዲሁም የካሳ ክፍያ ፈተናዎች ያጋጠሙ ቢሆንም፣ የተቀናጀ አመራር በመስጠት ችግሮቹን በመቅረፍ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ ተሠርቷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተያዘው የ2019 በጀት ዓመትም ይህንን የልማት ጉዞ አጠናክሮ በመቀጠል የኃይል ማመንጨት አቅሙን ወደ 9,770 ሜጋ ዋት ለማሳደግ እና 121.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል።

አባዲ ወይናይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: