Search

የዜጎችን ክብር እና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ውጥኖች

ዓርብ ነሐሴ 22, 2018 211

የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ እውን የሚሆነው የልማት ሥራዎች ማዕከል ሰው ሲሆን ብቻ ነው።

የሰው ልጅ የልማት መዳረሻም ምንጭም ነው እንዲሉ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያላስቀደመ ግንባታ ዘለቄታ አይኖረዉም።

በመደመር እሳቤ እየተተገበሩ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ውጥኖችም ይኸንኑ እውነት በተግባር በማረጋገጥ የሀገርን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር የነዋሪዎችን የኑሮ ተስፋ እና ክብር ከፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ለነገ ብቁ እና ንቁ ትውልድን ለማፍራት ዛሬ ላይ መሥራት የግድ መሆኑን የተረዳው የመደመር መንግሥት፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሰው ተኮር በሆነው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ላይ በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው።

ትምህርት ቤት የተዘረጋው ይኸው የምገባ ሥራ ሕፃናት የረሃብ ስሜት ሳይጫናቸው በትምህርታቸው ላይ ብቻ አተኩረው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እያስቻለ ይገኛል።

ይህ ጥረት ለተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ የመማር ፍላጎታቸውን ከማነሳሳቱም በላይ በኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ለነበሩ በርካታ እናቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር "በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ" እንዲሉ እጥፍ ድርብ ፋይዳ አስገኝቷል።

እናቶች ልጆቻቸውን በሥነ ሥርዓት እየመገቡ እና እየተንከባከቡ ለትምህርት ሲሸኙ የሚሰማቸው ደስታ በቤት ውስጥ ተቀምጠው የነበሩ ዜጎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ካስቻለው ዕድል ጋር ተዳምሮ ማኅበራዊ እርካታን ፈጥሯል።

በሌላ በኩል የኮሪደር ልማት ሥራዎች መሠረተ ልማትን ከከተማ ውበት እና ከነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር ያጣመሩ ሰው ተኮር ክንውኖች ናቸው።

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ ከጥቂት ጊዜያት በፊት በቆሻሻ፣ በአቧራ፣ በፍሳሽ ችግር እና በመጫወቻ ቦታ እጦት ይፈተኑ የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ ወደ ተንጣለሉ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ ወደ አረንጓዴ ስፍራዎች እንዲሁም ወደ ልጆችና አዛውንት መዝናኛ ሜዳዎች ተቀይረዋል።

ይህ ለውጥ አካባቢን ከማስዋብ አልፎ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ የሸማቾች አገልግሎት ማቅረቢያ እና የኅብረተሰቡን አእምሮ የሚያድስ ምቹ ከባቢ ሆኗል።

ከትምህርት ቤት ምገባ እስከ ከተማ ውበት እና መልሶ ማልማት የተዘረጉት እነዚህ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች፣ በዜጎች ልብ ውስጥ የይቻላል መንፈስን እያሰረጹ ያሉ ተጨባጭ የታሪክ አሻራዎች ናቸው።

ሰው ተኮር ልማቶቹ የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት እያሻሻሉ፣ ማኅበራዊ ትስስርን እያጠናከሩና የነገዋን ሀገር በጠንካራ መሠረት ላይ እየገነቡ ወደፊት መጓዛቸውን ቀጥለዋል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: